በተባበረ ክንድ የጠላትን ጥቃት በመመከት የሀገራችንን ሠላም እናረጋግጣለን - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ - ኢዜአ አማርኛ
በተባበረ ክንድ የጠላትን ጥቃት በመመከት የሀገራችንን ሠላም እናረጋግጣለን - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
ሚዛን አማን፣ ጳጉሜ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተባበረ ክንድ ጠላት የከፈተውን ጦርነት በመመከት የሀገራችንን ዘላቂ ሠላም እናረጋግጣለን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው እንዳሉት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱ ላይ ለ3ኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት በብቃት በመመከት የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ መስዋእትነት እየከፈሉ ነው።
"የተቃጣውን የአሸባሪ ቡድን ጥቃትና ወረራ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር ሆነን በተባበረ ክንድ በመመከት የሀገራችንን ሠላም እናረጋግጣለን" ብለዋል።
"እንደ ክልል የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ ከልማት ተግባራችን ጎን ለጎን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
"የክልላችን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በመንቀሳቀስ ጦርነቱን ለመመከት የሚደረገውን ትግል በደጀንነት ለመደገፍ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ለሀገር ክብርና ሠላም ቅድሚያ የሚሰጥ ህዝብ መሆኑን ማሳያ ነው" ሲሉ አክልዋል ።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ወራሪውን ቡድን ለመመከት የሚያደርጉትን ትግል በመደገፍ እረገድ ህዝቡ እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።
ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና የትግራይ ህዝብ የህወሓት የሽብር ቡድን ጦርነትን በመተው ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ግፊት ሊያደርጉ እንደሚገባም አመልክተዋል።
"አዲሱ ዓመት እንደ ክልል የጀመርናቸውን ሰፋፊ የልማት፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተግባር ፈጽመን የህዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ የምንችልበትና እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየተፈታተኑን ያሉ የሠላም ዕጦት ችግሮችን የምንፈታበት ዘመን እንደሚሆን እምነቴ ነው" ብለዋል፡፡
በዓሉ የተቸገሩትን በመርዳት በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን በማቋቋም የምናከብርበት መሆን እንደሚገባ በመግለጽ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተመኝተዋል።