ቀጥታ፡

ለመጪው አዲስ ዓመት በዓል የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ ለማቅረብ ዝግጅት ተጠናቋል

ጳጉሜን 04 / 2014(ኢዜአ) ለመጪው አዲስ ዓመት በዓል የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ለበዓሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ እንዳይኖር ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጿል።

በበዓል ወቅት የኃይል ፍላጎቱ ከፍ የሚል መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም መጪው በዓል በኃይል አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ችግር እንዳይገጥም ምን ዝግጅት እንደተደረገ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጪው በዓል የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

በኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ አስፈላጊው ፍተሻ መደረጉን ጠቁመው ጣቢያዎቹ ያለምንም ችግር ኃይል ማቅረብ የሚቻልበት ቁመና ላይ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ በፊት በነበሩ በዓላት የኃይል ፍላጎት ምን እንደሚመስል ጥናት እንደተካሄደ አስታውሰው ከዚህ በፊት የሚቀርበው ሃይል 2 ሺህ 700 ሜጋ ዋት በታች መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ በዓል ግን ከዛ ከፍ ያለ ኃይል ለማቅረብ ታቅዷል ያሉት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት 3 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ ዝግጅት እንደተደረገም አብራርተዋል።

ከተያዘው እቅድ የበለጠ ፍላጎት እንኳን ቢመጣ ማቅረብ እንደሚቻል አመልክተው ይህንን ለማድረግ በእያንዳንዱ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ 'ዲዚል ጀኔሬተሮች' ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በዓላት ሲመጡ ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች እንዳይጠቀሙ አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሞገስ በአሁኑ ግን የተደረገው ዝግጅት ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች ጭምር ያለምንም ችግር ኃይል መጠቀም የሚችሉበት በቂ የኃይል አቅርቦት ዝግጅት እንደተደረገ ተናግረዋል።

ኃይል ማመንጨት የጀመሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለቱ 'ዩኒቶች' የኃይል አቅርቦት ከፍ እንዲል እንዳደረገውም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው 'ኮርፖሬት'፣ በ'ሪጂኖች'፣ በ'ዲስትሪክት'ና በአገልግሎት መስጫ ማዕከል ደረጃ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በመለየት ቅድመ መከላከል ጥገና ስራዎች እንደተሰሩ በመግለጽ።

የዛፍ ቅርንጫፎች የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን እንዳይነኩ የመቁረጥ፣ የዘመሙ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎችንና መስመሮችን የማስተካከል ተግባራት መከናወኑን አስረድተዋል።

የኃይል ጭነት የሚበዛባቸው ቦታዎችን የማመጣጠን ስራዎች መሰራቱንም ጠቅሰው አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

አሁን ያለው 'ኔት ወርክ' በጣም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ አሁን ያለውን የደንበኞች ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ደረጃ ላይ አለመሆኑን በማመላከት።

ኔትወርኩን ማሻሻል እንደሚጠይቅ የገለጹት አቶ መላኩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሰባት ዋና ዋና ከተሞች የኔት ወርክ ማሻሻያ ስራዎች መከናወኑን ጠቁመዋል።

በወላይታ፣ ሻሸመኔ፣ ሀረር፣ ደብረማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ከተሞች ላይ ኔትወርክ ማሻሻልና መልሶ ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ዝርፍያ እየተፈጸመ የአገልግሎት መቋረጦች የሚከሰቱበት ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት አቶ መላኩ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መጠበቅ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም