ቀጥታ፡

ዞኖቹ ለመከላከያ ሰራዊት ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

ሚዛን አማን/ዲላ፣ ጳጉሜ 04/2017 (ኢዜአ) .የካፋና ጌዴኦ ዞኖች ለሀገር ህልውና መከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት  ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሰንጋና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ አበረከቱ ፡፡ 

ድጋፉን የየዞኖች አስተዳደርና የሴቶች አደረጃጀቶች ያዘጋጁት ሲሆን የእርድ ከብቶችና ሌሎች ቁሳቁሶችንም ያካተተ ነው።

የካፋ ዞን አስተዳደር ለመከላከያ ሠራዊት  ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የሰንጋና ሌሎች ቁሳቁሶች  ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ናቸው።

ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር እየተዋደቀ ላለው መከላከያ ሰራዊት ከሞራል ባለፈ በአይነት ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የዞኑ ህዝብ የበኩሉን በማድረግ ለሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል ።

ድጋፉ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች  የተሰበሰበ መሆኑንምእንዲሁ፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ 181 ሰንጋዎች እና 27 በጎችን ከህብረተሰቡ መሰብሰብ መቻሉን አቶ እንዳሻው አንስተዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው ሁሉም አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነቅቶ በመጠበቅ ለሠላሙ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክልል ማዕከል ተቋማት  አመራሮችና ባለሙያዎች  ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት የስንቅ ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊት  አበርክተዋል።

በክልሉ ሴቶች ሊግ አስተባባሪነት የተሰበሰበው ይህ የስንቅ ድጋፍ ለሰራዊቱ አለኝታነት ማሳያ እንደሆነም ተገልጿል።

የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪና የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ "ለሠላም የተዘረጉ እጆችን ለጠመዘዙ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ ምርጫቸው መመለስ  ልምዳችን ነው" ብለዋል።

ክልሉ ምንም እንኳ በቅርቡ የተደራጀ ቢሆንም ከሀገር የሚበልጥ ነገር ባለመኖሩ ቅድሚያ ሰጥቶ ሰራዊቱን እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

በበዓል ወቅት የዘማች ቤተሰቦችን መጠየቅና ማበረታታት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ድጋፉ ከ500 ሺህ በሚበልጥ ወጪ የተዘጋጀ ጥራጥሬ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ውሃ፣ ስኳርና የምግብ ዘይት  ሲሆን ለሴት የሰራዊት አባላት የሚሆን የንፅህና መጠበቂያም በድጋፉ መካተቱን ጠቅሰዋል።

በሌላ ዜና ለመከላከያ ሰራዊት 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ከጌዴኦ ዞን መደረጉን ያስታወቁት ደግሞ  የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ ናቸው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የዞኑን ህዝብ በማስተባበር 207 በግና ፍየል እንዲሁም 102 የእርድ ሰንጋዎችን ለድጋፍ ማዘጋጀት መቻሉንም አክለዋል።

በተጨማሪም በዞኑ ሴቶች በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ 800 ኩንታል በሶና ቆሎ የተካተተ ሲሆን ድጋፉ ባጠቃላይ 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት መሆኑንም አብራርተዋል።

የዞኑ ህዝብ ከዚህ ቀደምም ለመከላከያ ሰራዊት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በድጋፉ ለተሳተፈው የዞኑ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

የዞኑ ህዝብ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም