አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጋራ በማለፍ ለሰላምና ልማት የሚተጉበት እንደሚሆን እምነታቸን ነው-የሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጋራ በማለፍ ለሰላምና ልማት የሚተጉበት እንደሚሆን እምነታቸን ነው-የሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ ጳጉሜን 4/2014 (ኢዜአ) አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በማለፍ ለሰላምና ልማት በአንድነት የሚሰሩበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት እምባሳደሮች ገለጹ፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ለኢትዮጵያዊያን የመልካም አዲስ ዓመት ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የ13 ወራት አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ በየዓመቱ መስከረም 1 ቀን ወይም በጎርጎሪዮሳዊያን አቆጣጠር መስከረም 11 የዘመን መለወጫ በዓሏን ታከብራለች፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአዲስ ዓመት ተስፋን የሚሰንቁበትና ጥላቻና ቂምን በይቅርታ የሚሻገሩበት ልዩ እለት ነው፡፡
ከኢትዮጵ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ኢትዮጵያዊያን በመጪው አዲስ ዓመት በተባበረ መንፈስ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ አገርን ለማስቀጠል የሚሰሩበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርክሂን አዲሱ ዓመት ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የጤና፣ የብልጽግና፣ የፍቅር እና የደስታ እንዲሆን የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያውያን የገጠሟቸውን ፈተናዎች በብቃት የመወጣት አቅም ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን መልካም ገጽታና እሴት የሚያስተዋውቁበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በጋራና በትብብር መንፈስ የተሻለች አገር እንዲገነቡ እድል እንሚፈጥር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ኢትዮጵያዊያን አዲስ ተስፋ የሚሰንቁበት ጊዜ ነው” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የአየር ላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብሬናን ናቸው።
ዓመቱ የኢትዮጵያዊያን ሰላምና መረጋጋትን እንዲሁም አንድነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት የተሟላ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት ምኞታቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሄይኮ ኒትስሽኬ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት አገራቸውን በተባባረ ክንድ ወደተሻለ ፖቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፤ አዲሱ ዓመት ለመላ ኢትዮጵዊያን የሰላምና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።