ልዩነትን በመፍታት ለአንድነት ጠንከሮ መስራት ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነትን በመፍታት ለአንድነት ጠንከሮ መስራት ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ
አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 ኢትዮጵያ ለሌሎች አርአያ የምትሆን ጠንካራ አገር ለማድረግ ልዩነቶች በመፍታት በጋራ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። የኢህአዴግና ኦህዴድ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የጥፋት ኃይሎችም ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አቢይ አህመድ ዛሬ በተጀመረው ዘጠነኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ለኢትዮጵያም ህዝብ የሚያስፈልገው አንድነት ብቻ ነው። ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ህዝብ እርስ በእርሱ በመከፋፈሉ ምክንያት ነፃነቱን አጥቶና መብቱ ተረግጦ መቆየቱን አስታውሰው፤ አንድ መሆን ባለመቻሉም 'ኦሮሞ ማስተዳደር አይችልም' የሚል ሀሳብ ሲነዛ መቆየቱን ተናግረዋል። 'ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም" ለሚሉ ኦሮሞ አገር መምራት ብቻ ሳይሆን አገር መገንባት እንደሚችል በተግባር እንደሚያረጋግጥ ተናግረው፤ ኦሮሞ ገዳን ለዓለም እንደ ሰጠ ሁሉ በቅርቡ "አዲስ ፍልስፍና ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሰጥቶ ሊያሳያቸው ይፈልጋል" ብለዋል። አያሌ ድርጅቶች በኦሮሞ ስም ተደራጅተዋል "ይህ ደግሞ አንድ ሆኖ በጠነከረ ሃሳብ መስራት እንዳይቻል ምክንያት ሆኗል" ሲሉ ገልፀዋል። ስለዚህ ፓርቲዎች ቢበዛ ወደ ሁለት በመምጣት ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው መክረዋል። ከዚህም ሌላ የኦሮሞ ህዝብ ከራሱ አልፎ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ ተቻችሎ የመኖር ታሪኩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የጉዲፈቻ ስርዓትን የመሰረተ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በአንድነትና በፍቅር አቅፎ የሚኖር ህዝብ እንጂ የሚገድልና የሚያፈናቅል ያለመሆኑን ነው ያረጋገጡት። እንደአባጅፋር ያሉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸው በርካታ የኦሮሞ ጀግኖች መሆናቸውን አድዋ ምስክር መሆኑን አስረድተዋል። የኦሮሞ ህዝብ ያገኘውን ለውጥ የማይፈልጉ በኦሮሞም ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን የገለፁት ዶክተር አብይ፤ ከዚህ ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል። በህዝቡ ስም ለእኩይ ተግባር የምትንቀሳቀሱም ከጠላት ለይተን አንመለከታችሁም ሲሉ ተደምጠዋል። የኦሮሞ ህዝብም የተገኘውን እድል ተጠቅሞ ልማትን ማረጋገጥ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ድርጅቱ "በአዲስ አወቃቀር፣ ወጣትና በሳል መሪዎችን ያስቀምጣል፤ ሌሎች እህት ድርጅቶችም ይህን መከተል ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል። ዲሞክራሲን ያለስራ ፈጠራና፣ የኢኮኖሚ እድገት ማስፋት ስለማይቻል የስራ ፈጠራ ማሰፋትና የዜጎችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በስፋት እንደሚሰራ ገልፀዋል። በሰላምና በአንድነት በመቆም ለአገር ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር አርአያ የሚሆን ስራ መስራት እንደሚቻል አስታውቀዋል። ለዚህ ሂደት ጉልበት ሳይሆን የሃሳብ ልዕልና የመሪነቱን ቁልፍ ሊይዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።