ለሠራዊቱ እያደረጉትን ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃራ ከተማ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለሠራዊቱ እያደረጉትን ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃራ ከተማ ወጣቶች ገለጹ
ወልዲያ፤ ጳጉሜን 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገርን ከብተና ለማዳን የምንቆጥበው ገንዘብና ጉልበት የለም ያሉ የሃራ ከተማ ወጣቶች በቆቦ ግንባር የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን እየተፋለመ ላለው የወገን ጦር የጀመሩትን እገዛ እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።
የሃራ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ወጣቶቹ ለሠራዊቱ ምግብ በማዘጋጀት፣ የእርድ እንስሳትን አዘጋጅቶ በማቅረብ፣ አካባቢያቸውን በመጠበቅና ህዝብ በማስተባበር እየደገፉ መሆኑን አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሃራ ከተማ ወጣቶች እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን ዓላማ ለማሳካት ሃራ ከተማን መረማመጃ ለማድረግ እየጣረ ነው።
ይሁን እንጂ እሱን ጨምሮ የከተማዋ ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ የህወሓትን ወረራ በመመከት የበኩላቸውን እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች ተቀናጅተን ለጸጥታ ሃይሉ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ድጋፎችን በማጓጓዝና ተያያዥ ሥራዎችን በመስራት አጋርነታችንን እያሳየን ነው ብለዋል።
ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሠራዊቱ ጎን ሆኖ የጀመሩትን እገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ሀገርንና ወገንን ከብተና ለማዳን የሚቆጥቡት ገንዘብና ጉልበት አለመኖሩንና የህወሓት እኩይ ተግባር ሙሉ በሙሉ እስከሚቀለበስ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሃራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ሰኢድ እንደገለጹት በግንባር ለሚፋለመው ሠራዊት የከተማው ህዝብ አደረጃጀት በመፍጠር የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
"ለሠራዊቱ ትኩስ ምግብ በማዘጋጀት፣ ከሌላ አካባቢዎች የሚመጣውን የእርድ እንስሳትና ሌሎች የምግብ አይነቶች አዘጋጅቶ በማቅረብ እየደገፈ ይገኛል" ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች አካባቢያቸውን ከሰርጎገቦች ነቅቶ ከመጠበቅ ባለፈ በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና ህዝብ በማስተባበር የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ነው አቶ ሙሐመድ ያመለከቱት።
"የህዝቡ የደጀንነት ሚና መከላከያ ሠራዊታችንና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በሞራል፣ በጀግንነትና በቁርጠኝነት ጠላትን እንዲፋለሙ ሞራል ሆኗቸዋልም" ሲሉም ገልጸዋል።
ወራሪው የህወሓት ቡድን ዳግም አከርካሪው ተመትቶ እስኪደመሰስ ድረስ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ በትኩረት መስራቱን እንደሚቀጥል ከንቲባው አመልክተዋል።