ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት አገራትም የብርሃን ምንጭ በመሆኑ እንደ ፕሮጀክት ባለቤት እንደግፈዋለን-የኬኒያና ደቡብ ሱዳን ልዑክ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት አገራትም የብርሃን ምንጭ በመሆኑ እንደ ፕሮጀክት ባለቤት እንደግፈዋለን-የኬኒያና ደቡብ ሱዳን ልዑክ አባላት
ጷጉሜን 4/2014/ኢዜአ/ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለጎረቤት አገራትም የብርሃን ምንጭ በመሆኑ እንደ ፕሮጀክት ባለቤት እንደግፈዋለን ሲሉ ግድቡን የጎበኙ የኬኒያና ደቡብ ሱዳን ልዑክ አባላት ተናገሩ።
የቀድሞ የናይሮቢ ከተማ ከንቲባና የኬኒያ-ኢትዮጵያ ወዳጆች ማኅበር ሊቀመንበር ጆ አኬችና የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ወጣቶች ኀብረት ዋና ፀሐፊ ጀስቲን ኡሪዮ አጅንጎ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከጎበኘው የናይል ተፋሰሱ አገራት ልዑክ አባላት መካከል ናቸው።
"ግድቡን ለማየት በመታደሌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ' ያሉት ጆ አኬች፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ብትገነባውም ፋይዳው ከኢትዮጵያ ባሻገር ቀጠና አቀፍ በመሆኑ የአፍሪካዊያን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ለአብነትም ኬኒያና ኢትዮጵያ የኅይል ሽያጭ ስምምነቶችን ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው አገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ትስስር የሚበጅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ስቲን ኡሪዮ አጅንጎ በበኩሉ ግድቡ የቀጣናውን አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ሀብት መሆኑንና ጨለማ ውስጥ ላለችው አፍሪካ ብርሃን የሚፈነጥቅ ፕሮጀክት ነው ይላል።
ደቡብ ሱዳን ካላት መሬት 90 በመቶው የሚሆነው ለግብርና ስራ ምቹ መሆኑን ጠቅሶ፤ አሌክትሪክ ኅይል ካገኘች ያላትን ለም መሬት በመስኖ በማልማት "የአፍሪካ ዩክሬን" መሆን ትችላለች ነው ያለው።
እንደ ኬኒያ ሁሉ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ የኅይል ሽያጭ ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውሶ፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሁሉም የቀጣናው አገራት ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ባለቤቶች ሁላችን ነን ብሏል።
ግድቡ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ የገንዝብ ተቋም ድጋፍ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ሀብት የሚገነቡት መሆኑ ደግሞ ለአፍሪካዊያን ተምሳሌት እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡
ግድቡ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት በራሳችው አቅም መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ ጆ አኬች ገልጸዋል።
ጀስቲን ኡሪዮ በበኩሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ካለው ቀጣናዊ ፋይዳ እንጻር፤ ለተፋሰሱ አገራት የድጋፍ ጥሪ ከቀረበ የደቡብ ሱዳን ወጣቶች የአቅማችንን በማዋጣት ግድቡ እስኪጠናቀቅ ማገዝ ፍላጎት አለን ይላል ጀስቲን ኡሪዮ።