"የኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኞች በጦርነቱ የተፈጠሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ህዝብና አገርን አገልግለዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል" -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
"የኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኞች በጦርነቱ የተፈጠሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ህዝብና አገርን አገልግለዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል" -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
ጳጉሜን 04 ቀን 2014(ኢዜአ)"የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኞች በ2014 ዓ.ም በጦርነቱ የተፈጠሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ህዝብና አገርን አገልግለዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል" ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።
ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ ለነገ ተስፋ የሰነቁ በርካታ ስራዎችን ያከናወነች ሲሆን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ጦርነት ደግሞ ኢትዮጵያዊያንን በጋራ የፈተነ ተግዳሮት መሆኑ ይታወቃል፡፡
አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ሰላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመጨፍጨፍ ባለፈ በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡
በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የመሰረተ ልማት አውታሮች መካከል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በወቅቱ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ሌሎች የሃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ነጻ ማውጣታቸውን ተከትሎም አፋጣኝ የጥገና ስራ በማከናወን ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዓመቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ከፍተኛ ስራ ማከናወናቸውንም ነው የጠቀሱት፡፡
በተለይ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የኃይል አቅርቦቱን መልሶ ለማስጀመር ያከናወኑት ስራ የሚያስመሰግን መሆኑን አንስተዋል፡፡
አቶ ሞገስ የተቋሙ ሰራተኞች ጦርነቱ የፈጠረውን የስነ-ልቦና ጫና ተቋቁመው አገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በህብረተሰቡና በተቋሙ መካከል መተማመን ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮተቤ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታነህ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ተጠባባቂ ኃይል በመመደብ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከደንበኞች ኃይል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በቀን እስከ ሦስት ዙር ፍተሻ ይደረጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሪልታይም ግሪድ ኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ጉልላት እንግዳ በበኩላቸው በአገሪቷ 189 መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ 24 ሰዓት የቁጥጥር ስራዎች እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከፍተኛ መስመሮች ላይ ብልሽት በሚያጋጥምበት ወቅትም በፍጥነት ጥገና በማድረግ ወደ አገልግሎት ማስገባት ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል።