የሀድያ ዞን አስተዳደር ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የእርድ እንስሳት እና ደረቅ ስንቅ ለሠራዊቱ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሀድያ ዞን አስተዳደር ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የእርድ እንስሳት እና ደረቅ ስንቅ ለሠራዊቱ ድጋፍ አደረገ
ሆሳዕና ጳጉሜን 4/2014 (ኢዜአ) የሀድያ ዞን አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የእርድ እንስሳት እና ደረቅ ስንቅ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረገ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት በተለያዩ ችግሮች ብትፈተንም በጀግኖች ልጆቿ ህልውናዋ ጸንታ እስከዛሬ ቆይታለች።
“ለሚገጥሙ ችግሮች እጅ በማይሰጡ ክንደ ብርቱ ልጆቿ ነፃነቷን ሳታስደፍር በአንድነቷ መዝለቅ ችላለች” ብለዋል።
ዛሬም በወራሪው ህወሓት ሀገር ወቅታዊ ችግር ቢገጥማትም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብሯን ጠብቆ ለማቆየት ጠላትን እየተፋለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገርና ለህዝብ ብሎ ውድ ህይወቱን ጭምር እየከፈለ ያለውን ይህን ሠራዊት አለንልህ ለማለት የዞኑ ህዝብም በተለያየ መንገድ ድጋፉን እያሳየ መሆኑን አቶ አብርሀም ገልጸው፣ "ህዝቡ በአጭር ጊዜ ያሳየው ተነሳሽነት የሚያስመሰግን ነው" ብለዋል።
አስተዳዳሪው እንዳሉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ በተላላኪያቸው ህወሓትና በተለያየ መንገድ እጅ ለመጠምዘዝ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፀጋዬ ተረፈ በበኩላቸው “የሀድያ ህዝብ ለሀገር ሰላምና ህልውና መጠበቅ ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ የሚታወቅ ነው” ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ጦርነት ካወጀበት ጊዜ አንስቶ የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በዛሬው እለትም የዞኑ ህዝብ፣ ባለሀብቶችና የሃይማኖት ተቋማት ለመከላከያ ሠራዊቱ ከ42 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 892 የእርድ እንስሳት፣ 1 ሺህ 323 ኩንታል በሶ፣ ቆሎ፣ ስኳርና ኩኪስ ድጋፍ ማደረጉን አስታውቀዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ እድል ፈጠራ ሀላፊ አቶ በየነ ሻንቆ በበኩላቸው፣ "የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደጎን በመተው ጦርነት የከፈተውን የህወሓት ቡድን እየተፋለመ ላለው ሠራዊት የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ የጀመረውን ድጋፍ ያጠናክራል" ብለዋል።
በሆሳዕና ከተማ ሊች አምባ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ገብሬ ሚራጎ “የአሸባሪውን ቡድን ዓላማ ለማምከን በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ለመድረግ ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
የቀበሌው ነዋሪ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ የሚሆን በሁለት ቀናት ውስጥ 10 ሠንጋዎችን ጨምሮ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያየ ቁሳቁስ በማሰባሰብ ማስረከቡን ጠቁመዋል።
የሽብር ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያረጋገጡት።