የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስንቅና የበዓል ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስንቅና የበዓል ድጋፍ አደረጉ
ጷጉሜን 3/2014/ኢዜአ/ የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስንቅና የበዓል ድጋፍ አድርገዋል።
በምክትል ኘሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ፤ ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ድጋፉን አስረክበዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዓሉን የሚያከብርበት 1 ሺህ 329 ሰንጋዎች፣ 200 በግና ፍየሎችን ጨምሮ የስንቅና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ሲሆን ድጋፉ አጠቃላይ በገንዘብ ሲተመን 101 ሚሊዮን ብር ይሆናል።
በክልሉ ከሚገኙ ከሁሉም ከተሞችና ዞኖች የተሰበሰበ ድጋፍ ስለመሆኑም ወይዘሮ መስከረም ገልጸዋል።
የሰላም አጆች ተዘርግቶለት 3ኛ ዙር ጦርነት የከፈተውን አሸባሪ ህወሓት እየመከተ ላለው ጀግና ሰራዊት ድጋፍ በማድርጋችን ተደስተናል ብለዋለ።
ድጋፉ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ያሉት ሀላፊዋ ጦርነቱ እስኪቀለበስ ደረስ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ድጋፍና አብሮነታችን ይቀጥላል ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም ግንባር ተሰልፎ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን በተግባር ማሳየቱን ቀጥሏል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሁሉም ከተሞችና ዞኖች በዛሬው እለት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው የሌሎችም ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።