የንግድ ስራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ስራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል

አዳማ ፣ ጳጉሜ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የንግድ ስራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ የስራና ክህሎት ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው በንግድ ስራ ውድድር የተሻለ ሃሳብና የፈጠራ ስራ ይዘው በመቅረብ በውድድር ላሸነፉ ወጣቶች እውቅና ሰጥቷል።
የኦሮሚያ የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ኢንድሪስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በድህነት ቅነሳ ተግባራት ውስጥ የንግድ ስራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ለመደገፍና ለማብቃት ግብ አስቀምጠው እየሰሩ ይገኛሉ።
በአዲሱ የበጀት ዓመት የተሻለ የንግድ ስራ ውድድርና ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለመደገፍ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መዘጋጀቱን ሃላፊው ገልጸዋል።
ገንዘቡ በንግድ ስራ ፈጠራ የተሻለ ሙያና ብቃት ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶች በውድድር በመለየት ወደ ስራ ለማስገባት የሚውል ነው ያሉት አቶ አህመድ፣ ወጣቶችና ሴቶች ይህን አውቀው በንግድ ስራ ፈጠራ ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
ዛሬ የተካሄደው የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ዓላማው ለራሳቸው ስራ የፈጠሩና ለሌሎች ስራ አጦች የስራ አማራጭ የዘረጉ ወጣቶችና ሴቶችን ለማበረታታት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ማዕከል ዲን ዶክተር ተመስገን ደበሎ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የንግድ ስራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶች በማወዳደር አሸናፊዎችን መለየቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች በአቅም፣ በክህሎት፣ በሙያና እውቀት ለማብቃት በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ዩኒቨርሲቲው ሙያቸውን ለማስፋፋት የሚያግዛቸውን የመስሪያ ሼዶችና የእንስሳት ማደለቢያ ሰርቶ ለምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማ አስተዳደር ማስረከቡንም ገልጸዋል።
ከደረቅ ቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመስራትና ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ተወዳድሮ ለሽልማት መብቃቱን የተናገረው ደግሞ ከተሸላሚዎች መካከል ወጣት በረከት ደነቀ ነው።
በዚህም 1ኛ በመውጣት 100ሺህ ብር ተሸላሚ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት በረከት፣ ያገኘው ሽልማት የፈጠራ ስራውን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚያግዘው ገልጿል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ራቢያ ሃጫሉ እንደገለጹት በንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ማገዶ ቆጣቢ የእንጀራና የዳቦ መጋገሪያ ምጣድ በመስራት ውድድሩን አሸንፈው የ70 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
የፈጠራ ስራው የእናቶችን ጊዜ፣ ጉልበትና ማገዶ በመቆጠብ ረገድ የተሻለ ቴክኖሎጂ መሆኑንም አክለዋል።
በመድረኩ በፈጠራ ችሎታቸው ተወዳድረው 1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ላሸነፉ 12 ወጣቶች 1 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተሰጥቷል።
በተመሳሳይ 18 ለሚሆኑ ደግሞ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ተሳታፊ እንደሚሆኑም ቃል ተገብቶላቸዋል።