መንግስትና አሸባሪውን ህወሃት በእኩል ሚዛን ላይ ማኖር በፍጹም ተገቢነት የለውም- አምባሳደር ተሾመ ቶጋ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስትና አሸባሪውን ህወሃት በእኩል ሚዛን ላይ ማኖር በፍጹም ተገቢነት የለውም- አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
ጳጉሜን 3 ቀን 2014 (ኢዜአ)ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስትና አሸባሪውን ህወሃት በእኩል ሚዛን ላይ አኑሮ መመልከቱ በፍጹም ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍና የህዝብ ማእበል በማንቀሳቀስ በአማራና በአፋር ክልሎች ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቷል።
መንግስት ለሰላም ሲል የዘረጋውን እጅ በመተው መሳሪያ አንግቦና የሰው ማእበል አሰልፎ በመምጣት የእልቂት እና ውድመት ዓላማ አንግቦ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ አሸባሪው ህወሓት በጥፋት መንገዱ ቀጥሎ የሰላም ጠንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የጥፋት ቡድኑ ከድርጊቱ በተቃራኒ በመጮህ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ሆኖም አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ውጊያ በማቆም የመንግስትን የሰላም አማራጭ እንዲከተል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ማሳደር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ "አካፋን አካፋ የሚልበት እና አሸባሪውን ህወሓት አሸባሪ ብሎ" መጥራት ሲገባው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስትና አሸባሪውን ህወሃት በእኩል ሚዛን ላይ አኑሮ መመልከቱ በፍጹም ተገቢነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የአገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ እየጣረ ያለን መንግስትና በጦርነት አዙሪት ውስጥ ያለን አሸባሪ ቡድን ለያይቶ በመመልከት ለትክክለኛ ፍትህ መቆም ይገባል ብለዋል።
ሁሉንም የዓለም ማህበረሰብ በአንድ አይነት እይታ ውስጥ ናቸው ብሎ መፈረጅ ባይቻልም ብዙዎቹ ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ዘንግተውታል ብለዋል አምባሳደር ተሾመ።
በመንግስት በኩል አሁንም የሰላም እጆች እንደተዘረጉ መሆናቸውን ገልጸው አሸባሪው ቡድን ለዚህ በጎ ተግባር ጦርነት በማቆም ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት።
"የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ህብረት ሊደረግ የታሰበውን የሰላም ውይይት ከደገፈ እና አሸባሪውን ህወሓት ወደ ሰላም እንዲመጣ ጫና ካደረጉበት ግጭቱ በሰላም ሊፈታ እንደሚችል ተስፋ አለኝ" ብለዋል።