ቀጥታ፡

በ2015 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል

ጳጉሜን 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2015 በጀት አመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የግድቡን ቀሪ ግንባታ ለማከናወን ለሚያስፈልገው ተጨማሪ 60 ቢሊየን ብር የህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።

የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታገል ቀኑብህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያውያን እውቀትና ገንዘብ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል።

በሃብት ማሰባሰብ በኩል በ2014 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፤ በተያዘው 2015 በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።

የግድቡ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨቱና ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ የህብረተሰቡ ተሳትፎ መጨመሩንም ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ፍጻሜው 232 ቢሊዮን ብር እንደሚወስድ ገልጸዋል።

May be an image of 1 person, standing and indoor

የውጭ ምንዛሬ መጨመርና ሌሎች ምክንያቶች በግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ወጪዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመፈጠራቸው ግድቡን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ በጀት ማስፈለጉን አብራርተዋል።

በዚህም የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በፍትሐዊነት ለመጠቀም የወሰደቻቸውን ሀቀኛ ርምጃዎች ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ሚኒስቴሩ በ140 ሚሊዮን ብር የኢትዮጵያ መሪዎች የዓባይን ወንዝ ለመጠቀም የነበራቸውን እቅድና ጅምር እስከ አሁኑ የግድቡ ደረጃ የሚያሳይ የኤግዚቢሽን ማዕከል እየገነባ ነው ብለዋል።

ጉባኤው የምክር ቤቱን የ2014 በጀት ዓመት ስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ድጋፍ ማሰባሰብና ሌሎች ለግድቡ የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክረው የማስተባበር ሚናቸውን እንደሚወጡ የምክር ቤቱ አባላት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም