ቀጥታ፡

በክረምቱ የስፔስ ሳይንስና ተያያዥ የቴክኖሎጂ መስኮች የሰለጠኑ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎች ፈጠራዎች ለእይታ ቀረቡ

ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) በክረምቱ የስፔስ ሳይንስና ተያያዥ የቴክኖሎጂ መስኮች የሰለጠኑ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎች የስልጠና ጊዜ ፈጠራቸው ለእይታ መብቃታቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት "ስቲምፓወር ሴንተር" ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በስፔስ ሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፎች በክረምቱ ስልጠና የሰጣቸውን የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ታዳጊዎችን አስመርቋል፡፡

በአዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሃንና አምቦ ዩኒቨርስቲዎች ለሁለት ወራት ስልጠና የወሰዱ 10 ታዳጊዎች ናቸው የተመረቁት።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች የነገ ታላቅ ፈጣሪዎች በመሆናቸው በስልጠና አቅማቸውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ በፊትም ከባለድርሻ አከላት ጋር በመተባበር ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን አስታውሰው ዘንድሮም ተመሳሳይ ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር የእድሉ ተጠቃሚ ያልሆኑ ታዳጊዎችን ተደራሽ ለማድረግ እደሚሰራ ጠቁመዋል።

ታዳጊዎቹ የፈጠሯቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በምረቃ-ስነ ስርዓቱ ላይ ለእየታ ቀርበዋል፡፡

ከፈጠራ ስራዎቻቸው መካከል ለልማት ስራና በችግር ጊዜ ራስን ለመከላከል የሚያስችሉ እንደ ሮቦት፣ ቴሌስኮፕ ድሮን፣ ራዳር እና ሮኬት የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታ መቅረባቸውን ዘርዝረዋል።

ለቤተ ሙከራ፣ ለህክምና እንዲሁም የኑሮ ዘይቤን ለማሻሻል የሚጠቅሙ መተግበሪያዎችም የባለ ልዩ ተሰጥኦዎቹ ፈጠራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተሰጣቸው ስልጠና የፈጠራ ህልማቸውን ይበልጥ ለማሳደግና የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ ያስቻለ ነው ያሉት።

ከተመራቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳዎቸ በቀጣይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለውጥ እንድታመጣ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት በህዋ ሳይንስ ዘርፍ አብረው ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የስምምነቱ ዋና አላማ የሰው እና የገንዘብ ሃብቶችን በማቀናጀት በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ገልጸዋል፡፡

ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ዶክተር ለሚ ጉታ፤ ዩኒቨርሲቲያቸው በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው በመሆኑ በቅንጅታዊ ስራው የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

የስቲምፓወር ዳይሬክተር ዶክተር ስሜነው ከስክስ፤ በኢንስቲትዩቱ ለሚመጣ የትብብር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ በተመሳሳይ የስልጠናና ሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም