የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አባ ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አባ ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
ጷጉሜን 3/2014/ኢዜአ/ የቀድሞ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አባ ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል።
በስርአተ ቀብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጥንታዊ አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴን ጨምሮ የቀድሞ አርበኞችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡
በቀብር ስነ-ስርዓታቸው ላይ በተነበበው የህይወት ታሪካቸው ላይ እንደተገለጸውም ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርን ለ12 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እና በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከሌሎች ሀገር ወዳድ ጀግኖች ጋር በመሆን ለአራት ዓመታት በአርበኝነት አገራቸውን አገልግለዋል።
ለፈጸሙት የአርበኝነት ጀብዱም ከቀድሞ የጽሕፈት ሚኒስቴር ዲፕሎማ የተሰጣቸው ሲሆን ከድል በኋላም በመንግስት ተቋማት በተለያየ ሃላፊነት በቅንነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ በአስታራቂ ሽማግሌም ነበሩ።
የጥንታዊ አርበኞች ማህበር አባላት ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ የጥንታዊ አርበኞች ማህበር በሁለት እግሩ እንዲቆም በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን በስርአተ ቀብራቸው ላይ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ገልጸዋል።
ለአባትና እናት አርበኞች መንግስትንና ህዝብን አስተባብረው የመኖሪያ ቤት እንዲገነባ በማድረግም ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በተጨማሪም አርበኞች በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ ህክምና እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ከአባታቸው አቶ አባተ ወርቁ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ሹሜ አያሌው ግንቦት 1922 ዓ.ም በጋይንት ነበር የተወለዱት፡፡
አባ ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጳጉሜን 02 ቀን 2014 ዓ.ም በ92 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
ስርዓተ ቀብራቸውም በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።