ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ኃለፊነት ሊሆን ይገባል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጳጉሜን 3 /2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሰላምን በመገንባት፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዚደንቷ የጳጉሜን-03 የሰላም ቀን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ በተለያዩ ቋንቋዎች መልዕክቶችን የያዘውን "የሰላም ምሰሶ" መርቀው ከፍተዋል።

ከዑራኤል እስከ ወሎ ሰፈር ያለው መንገድም "የሰላም ጎዳና" በሚል ተሰይሟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስየላለፉት ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጳጉሜ-03 ሰላም ለኢትዮጵያ በሚል ተሰይሟል፤ ዓላማውም ለኢትዮጵያዊያንና ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ ታሪክ ሰሪ ኢትዮጵያውያንን የሚዘክርና የአፍሪካ አገራትን የሚገልጹ መንገዶች በመዲናዋ መሰየማቸውንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያዊያን ሰላም በማሰብ የተሰየመው የሰላም ምሰሶና ጎዳናም ሰላምን ለማሰላሰል ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ሰላም የሁሉ ነገር መፍቻ ቁልፍ መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ አመላክተዋል።

ምንም እንኳን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ባይታጡም ይህ ግን በምንም አይነት መልኩ ሰላም ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባው እንደማይችል ጠቅሰዋል።

ጦርነትና የጥይት ጩኸት በማቆም ብቻ ሰላም እንደማይመጣ ጠቁመው፤ የሃሳብ የበላይነትንና እውቀትን በማስቀደም ሰላም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።  

መቻቻል፣ መደማመጥና መከባበርን በማስቀደም ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ምልክቶች ሲታዩም በዝምታ ማለፍ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

የሃሳብ ልዩነትን በሃሳብ የበላይነት በመፍታት ሰላምን መገንባት፣ መንከባከብና ዘላቂ ማድረግም ይጠበቃል ነው ያሉት።

"ሰላም ከሰማይ የሚወርድ መና" ባለመሆኑ የሰላምን እሴቶች በመገንባት፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።  

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ኢትዮጵዊያን በተለያየ ጊዜ ለሰላም ሲሉ መስዋትነትን ከፍለው የአገራቸውን ሉዓላዊና አንድነት አስጠብቀው ማቆየታቸውን ገልጸዋል።

በታሪክ አጋጣሚ በዚህ ወቅት የሚገኝ ትውልድም አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል።

ለሰላም ሲባል የማይከፈል ዋጋ እንደሌለ በመጠቆም የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ  ለሰላም ያላትን ፅኑ ፍላጎት እንዲገነዘቡ እንፈልጋለን ብለዋል።

በዕለቱ የተሰየመው "የሰላም ምሰሶና ጎዳና" ኢትዮጵያ ያላት የሰላም መንገድ መሆኑን ለማሳየት ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው።

ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚላላኩ ቡድኖች የአገራችን ፍላጎትና ጎዳና የሰላም አማራጭ መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላም መምጣት ይኖርባቸው ብለዋል።

የጳጉሜ 3 የሰላም ቀን አስምልከቶ በከተማ ደረጃ የመዲናዋ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልቃድርን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌ፣ አባገዳዎችና ሌሎች አካላት በተገኙበት የሰላም ኮንፈርን ተካሂዷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም