ቀጥታ፡

የአገርና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለዘላቂ ሰላምና የሀገር ልማት ሁሉም በጋራ እንዲሰራ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

ጳጉሜን 3 /2014 (ኢዜአ) በአዲሱ አመት የአገርና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለዘላቂ ሰላምና የሀገር ልማት ሁሉም በጋራ እንዲሰራ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያውያን በአዲሱ አመት ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣የእርስ በእርስ ግጭትን፣ነፍጥ አንግቦ መዋጋትን በመተው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚሰሩበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የኃይማኖት አባቶች ተናግረዋል።

አዲሱ አመት ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ብልጽግና፣ አንድነት፣ መረጋጋት፣ እርስ በእርስ መተሳሰብ ይዞ የሚመጣ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፤በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የነበረው የሰላም መደፍረስ በሰው ልጆች ላይ ከባድ ዋጋ ማስከፈሉን አውስተዋል።

በመሆኑም በአሮጌው አመት ለሰላም እጦት ምክንያት የነበሩ ድርጊቶችን መቋጫ በማበጀት ለአገር ሰላምና አንድነት አዲስ እይታ ለማፍለቅ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለግል ዓላማና ጥቅም ብቻ በመስራት በአገርና ህዝብ ላይ የነበረው መከራና ግፍ አብቅቶ ለአብሮነት የሚሰራበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል።

በአዲሱ አመት የአገርና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለዘላቂ ሰላምና የሀገር ልማት ሁሉም በጋራ ይስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

"ሰላም በመስጠትና በመቀበል ላይ የተመሰረተ ከፈጣሪ የሚሰጥ ስጦታ ነው" ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እርስ በእርስ በመዋደድ፣በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና መከባበር ለዘላቂ ሰላም ሁሉም እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ መሃመድ፤ ቤተ እምነቶች እያከናወኑ ያለውን የሰላም እሴት ግንባታ ምዕመናንም ተከትለው ሊተገብሩት ይገባል ብለዋል።

May be an image of 1 person and standing

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምክትል ጠቅላይ ጸሃፊ አባ ገብርኤል ወልደሃና በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ጸሎት ለአገር ሰላምና መረጋጋት መሆን ይኖርበታል ይላሉ።

ይሁን እንጂ ሰላም የሁሉም ሰው ስራ ውጤት በመሆኑ ጦርነትና መፈናቀል እንዲያበቃ የአዲሱ ዓመት ቀዳሚ አጀንዳ ሰላም ማምጣት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ምክር የሚቀበልና ቁጣ የሚፈራ ትውልድ የሚበራከትበት ዓመት እንዲሆን የተመኙት ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው።

May be an image of 1 person

ሰላም አንድ ወገን ስለፈለገ ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ በመነጋገርና በመደማመጥ የጋራ አገርን በጋራ ለመገንባት ሁላችንም እንዘጋጅ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም