በናይል ተፋሰስ አገራት ጉባዔ ተሳታፊ አገራት የኢትዮጵያን ዕውነታ በአግባቡ መረዳት ችለዋል- የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
በናይል ተፋሰስ አገራት ጉባዔ ተሳታፊ አገራት የኢትዮጵያን ዕውነታ በአግባቡ መረዳት ችለዋል- የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ
ጳጉሜን 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ሰሞኑን የተካሄደው የመጀመሪያው የናይል ተፋሰስ አገራት ጉባዔ የተፋሰሱ አገራት የኢትዮጵያን ዕውነታ በአግባቡ እንዲረዱ ማስቻሉን የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴዎች ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች የተፋሰሱ አገራት ቀጣናዊ ትስስር የሚበጅና በራስ አቅም መተማመን አርዓያ የሆነ ፕሮጀክት መሆኑንም ማረጋገጥ ማስቻሉ ተመልክቷል።
ከተፋሰሱ አገራት ልዑካንን በማሳተፍ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የመጀመሪያው ናይል ተፋሰስ አገራት የናይል ውሃ ምክንያታዊና ፍትሐዊ አጠቃቅም ጉባዔ /አፍሪራን/ ጉባዔ ተጠናቋል።
ከተፋሰሱ አገራት የመጡ ተሳታፊዎችም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል።
የጉባዔው ፅንሰ ሃሳብ አመንጭዎችና የዝግጅቱ ኮሚቴ አባላት ለኢዜአ እንዳሉት በአዲስ አበባ የተደረገው 'አፍሪራን' ጉባዔ ስኬታማ እንደነበር አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል መምህሩ ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ፤ የጉባዔው ዓላማ በተፋሰሱ አገራት ምሁራንና አሳቢያንና ፖሊሲ አውጭዎች መካከል ጥናትን መሰረት ያደረገ ምክክር ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህም አገራቱ በዓባይ ውሃ ላይ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ውሳኔዎች ግብዓት የሚሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለመለዋወጥና ዓባይን ታሳቢ ያደረጉ ፖሊሲዎች እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አቡኔ መሐሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ አንትሪፖሎጂና ብዝሃነት ተመራማሪና የፓርላማ አባል ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው።
ከግማሽ ቢሊየን በላይ ከሚገመተው በናይል ተፋሰስ አካባቢ የሚገኘው ህዝብ በተፈጥሮ ጸጋ የታቀፈ፤ ነገር ግን ከግማሽ በላይ የሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንደሆነ ገልጸዋል።
የተፋሰሱ አገራት ፀጋዎችን ተቀራርበው የሚነጋገሩበት ዕድል አለመኖሩና እንዲመካከሩም ከውጭ ሃይሎች ሳንካ በመፈጠሩ ጸጋዎቻቸውን አልምተው መበልጸግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ጉባዔው በዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ የሚወሰደውን ትርክት መልክ የማስቀየር ዓላማ አለው ብለዋል።
የአዲስ አበባው ሰሞነኛ ጉባዔ በዓባይ ውሃ ለሁሉም የላይኛው ተፋሰስ አገራት የጋራ ሀብት በመሆኑ ማንም ሳይጎዳ ሁሉንም እንደ የፍላጎትና አቅማቸው ሁሉም በትብብር አልምተው ከድህነት የሚወጡበት ስርዓት እንዲፈጠር ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።
በተፋሰሱ ጉዳይ የሚፈጠሩ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ ለአፍሪካዊያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ በመፍታት ወደ ፊት መራመድ እንደሚገባ ልዑኩ ተስማምቷል ብለዋል።
የጉባዔው ተሳታፊዎችም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም የተገነባ፣ ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጎለበት የአፍሪካ ተስፋና መኩሪያ ፕሮጀክት በመሆኑ የትብብር እንጂ የጥል መንስኤ እንደማይሆን አረጋግጠዋል ብለዋል።
በአጠቃላይ ጉባዔው ስኬታማ እንደሆና በቀጣይም በሌሎች አገራት እየተዘዋወረ ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ በዓባይና በሌሎች ድንበር ዘለል ተፈጥሯዊ ሀብቶችን የማልማት ምክክሮች ይደረጉበታል ነው ያሉት።
የተነሱ ሃሰቦችም የውሃ ሀብትን በትብብር ማልማት እንደሚገባ፣ ሕዳሴ ግድብና መሰል ግድቦችም ቀጣናዊ አቅም መፍጠሪያ አፍሪካዊ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ በምክክሩም፣ በጉብኝት ወቅትም እንዳረጋገጡ ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አበራ እንደሻው፤ በናይል ተፋሰስ አገራት ምክንያታዊና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት ላይ በመከረው ጉባዔ ላይ ከሁሉም አገራት በሚባል ደረጃ ጥሪ የተደረገላቸው ጉባዔተኞች ታድመው ዕይታቸውን አጋርተዋል ብለዋል።
በተለይም በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይ አገራት በምን መልኩ እየተጠቀሙ ከድህነት መውጣት እንደሚችሉ የመማሪያ መደረክ በመሆኑ፤ ስኬታማ ጉባዔ እንደነበር ገልጸዋል።
ጎብኝዎቹ በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዓላማ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ሳይለቅ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ሁሉንም የቀጣናው አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጡ አስችሏል ብለዋል።
ግድቡ በተለይም ለአፍሪካዊያን የሚጠቅም፣ ኢትዮጵያን በራሳቸው ገንዘብ የሚሰሩት አርዓያ የሆነ፤ ፕሮጀክቱም ለአገራቱ መልከ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሉት ከፅንሰ ሃሳብ ባሻገር በአካል ተመልክተዋል ብለዋል።