በበጀት ዓመቱ በወጪ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ብድር ይቀርባል - ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ በወጪ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ብድር ይቀርባል - ብሔራዊ ባንክ
ጳጉሜን 03 /2014 (ኢዜአ) በ2015 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት በልዩ ሁኔታ በባንኮች በኩል የውጭ ምንዛሬ ብድር እንደሚቀርብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የቀርጫንሼ ግሩፕ 8ኛ አመት የምስረታ በዓልና የ2014 ዓ.ም አፈጻጸም ግምገማ መርሃ ግብር ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዶክተር አዱኛ ደበላ፣ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በወቅቱ እንዳሉት፤ የወጪ ንግድ ምርቱ ባለፉት ሦስትና አራት አመታት ከፍተኛ እድገት ያሳየ ሲሆን ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ቡና ዋናው ነው።
በወጪ ንግድ ዘርፉ ለተገኘው ውጤትም አርሶአደሮች፣ ላኪዎችና የፋይናንስ ተቋማት የክልልና የፌደራል አመራሮች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል። ቡናን ጨምሮ በአጠቃላይ ከወጪ ንግድ በ2014 በጀት አመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።
በዚህ በጀት አመትም አፈጻጸሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቡናን ጨምሮ በወጪ ንግድ ዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማት በባንኮች በኩል የተለየ ብድር ይቀርባል ነው ያሉት።
ይህም የተደረገው የወጪ ንግድ ዘርፉ ለሀገሪቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በመሆኑ ድጋፉን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የቀርንጫሼ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ እስራኤል ደገፋ ድርጅቱ ባለፉት ስምንት አመታት ከቡና ላኪዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸዋል።በ2014 በጀት አመትም ወደ ውጭ ከላከው የቡና ምርት 101 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል ብለዋል።
በቀጣይም ቡናን ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ድርጅቱ የተሻለ ገቢ ለማስገኘት እንደሚሰራ ተናግረዋል።በስምንቱ አመታት ከቡና ምርት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱና ከ56 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆናቸው ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ ወደ ውጭ ከተላከ 300 ሺህ ቶን በላይ ቡና 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወቃል።