ሕብረተሰቡ ለዘመን መለወጫ በዓል አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ደሕንነቱ የተረጋገጠ ሥጋ እንዲገዛ ቄራዎች ድርጅት አሳሰበ

ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) ሕብረተሰቡ ለመጪው አዲስ ዓመት የቄራዎች ድርጅት ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው ሉኳንዳ ቤቶች ደሕንነቱ የተረጋገጠ ሥጋ መግዛት እንዳለበት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አሳሰበ።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለ2015 የዘመን መለወጫ በዓል ሰባት ሺህ የበሬ፣ የበግና ፍየል ዕርድ እንደሚያከናውን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ እንድሪስ አስታወቁ።

May be an image of 1 person, standing and outdoors

የዕርድ ሥራውን ለማቀላጠፍ ከቋሚ ሠራተኞች በተጨማሪ ጊዚያዊና የኮንትራት ሠራተኞችንና ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

ኅብረተሰቡ የሕገ-ወጥ የእንስሳት ዕርድና የሥጋ ዝውውር ራሱን እንዲጠብቅም ዋና ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል።

አቶ ሰይድ ኅብረተሰቡ ከቄራዎች ድርጅት ካከራያቸው ሱቆችና ከሉኳንዳ ቤቶች የተመረመረ ሥጋ መግዛት እንዳለበትም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የበሬ ሥጋ በኪሎ በ435 ብር፣ የፍየል ስጋ 310 ብር ፣የበግ ስጋ 300 ብር ተምኖ ለመሸጥ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በዘመን መለወጫ በዓል ዕለትም ሙሉ በግና ፍየል እንደሚሸጥም ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የቁም እንስሳት እርድ አገልግሎት የሚፈልጉ ካሉ አዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በማምጣት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መዓዛ ቀለመወርቅ በበኩላቸው ማኅበሩ የእንስሳት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሥራ አስኪያጇ አክለውም ማኅበሩ ለ2015 ዘመን መለወጫ በዓል 10 ሺህ የሚሆኑ የቁም እንስሳትን ወደ መዲናዋ ለማስገባት ዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

ወይዘሮ መዓዛ በባዓል ገቢያ ምልከታቸው ዝቅተኛው የበሬ ዋጋ ከ20 ሺህ እስከ 40 ሺህ፣ መካከለኛው ከ40 ሺህ 65 ሺህ እና ከፍተኛው ከ65 ሺህ በላይ መሆኑን ተናግርዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም