ከመስከረም 1 ጀምሮ ሁሉም የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የግል ድርጅት ሰራተኞች ወደ ጡረታ ዐቅድ ማካተት ተግባራዊ ይሆናል

ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) ከመስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የሆኑ ሁሉም የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ወደ ጡረታ ዐቅድ ማካተት ሂደት ተግባራዊ እንደሚደረግ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አስታወቀ። 

በፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የሆኑ የግል ሰራተኞች ወደ ጡረታ ዐቅድ እንዲካተቱ በ2014 ዓ.ም መመሪያ የወጣው ውሳኔ ከመስከረም አንድ ጀምሮ በሁሉም የግል ድርጅቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጿል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ዋዩማ የውሳኔው አፈጻጻም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥና የማህበራዊ ዋስትናን አለማቀፋዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ የአዋጅ ማሻሻያ በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል። 

ከአዋጁ ማሻሻያ ውስጥ አንዱና መሰረታዊ የሆነው በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም በሌላ ስያሜ በሚጠራ ዐቅድ ተጠቃሚ የነበሩ ሰራተኞችን በግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ ዐቅድ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ መመሪያ የወጣ መሆኑን ገልጸው ከመጪው መስከረም አንድ ጀምሮ በሁሉም የግል ድርጅቶች ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል። 

የመመሪያው ተግባራዊ መደረጉ ከዚህ ቀደም በግል ድርጅት ሠራተኞች ዕቅድ ያልተሸፈኑ ሰራተኞች በጡረታ ዐቅድ የሚሸፈኑበትና የተጠራቀመ የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብ ለጡረታ ፈንድ ገቢ በማድረግ ቀደም ሲል የፈጸሙት አገልግሎት ለጡረታ አበል አወሳሰን እንዲታሰብ እንደሚያስችል አብራርተዋል። 

መመሪያው ከ2003 ዓ.ም በፊት በተቋቋሙና የግል ድርጅት ከነበራቸው ፕሮቪደንት ፈንድ የማህበራዊ ዋስትና ዐቅድ ተጠቃሚነታቸውን ለመቀጠል ወስነው የቀጠሉና በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ያልተሸፈኑ የግል ድርጅት ሰራተኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል። 

የፕሮቪደንት ፈንድ በሠራተኛው መደበኛ የወር ደመወዝ ላይ ተመስርቶ በየወሩ ተቀንሶና የአሰሪው ድርሻ ተጨምሮ ወይም በግል ድርጅቱ ብቻ በሚደረግ መዋጮ በድርጅቱ ወይም በሠራተኛው ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ የሚጠራቀም ገንዘብ ነው። 

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና በመስጠትና የዐቅድ አባል በማድረግ ሕገ መንግስታዊ መብታቸው የተረጋገጠና ምቹ የስራ አከባቢን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም