ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ፤ የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርገዋል።

የግድቡን የሲቪል ስራ፣ የኤሌክትሮ መካኒካልና የውሃ ማቀባበያ ወይንም የብረታ ብረት ስራዎችን በተመለከተ አፈጻጸሙን አብራርተዋል።

የሲቪል ስራዎች 96 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል 62 በመቶ መጠናቀቁን ጠቅሰው የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታ 9 ዩኒቶች ተፈብርከው ተከላ ላይ የሚገኙ ሲሆን 4ቱ በመጓጓዝና በፍብረካ ላይ ይገኛሉ ተብለዋል።

የውሃ ማስተላለፊያ የብረታብረት ስራዎች ከ73 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው የደን ምንጣሮም 40 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ2014 በጀት አመት ለግድቡ ግንባታ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን ከህዝብ በስጦታና ከቦንድ ግዥ 16 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም