የህዝብን ችግርና እያከበዱ ያሉ ቡድኖች ነፍጣቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ ቀረበ

89

ጳጉሜን 3/2014 (ኢዜአ) የህዝብን ችግር እያከበዱ ያሉ ቡድኖች ነፍጣቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የጳጉሜን ወር ሁሉም ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ሲሆን ዛሬ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን ተደርጎ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከወኑበት ይገኛል።

በዚህ ዕለት ስለ ሰላም አስፈላጊነት ስለ ሰላም ዕሴቶች ኢትዮጵያውያን ይነጋገራሉ፤ይመክራሉ፤ የተጣሉም በይቅርታ ዕርቅ የሚያወርዱበት ይሆናል።

በኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይና ችግሮችን በምክክር የመፍታት አስፈላጊነት ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኢትዮጵያ ላለፉት ረጅም ዓመታት በርካታ ግጭቶችን አስተናግዳለች ይላሉ።

በተለይም ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች ያደረሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

በአንድ ሀገር እየኖርንና ብዙ የሚያጋምዱን ጉዳዮች እያሉ፤ የ21ኛው ክፍለዘመን ከሚጠይቀው የሀሳብና የምክክር ሂደት ይልቅ ችግሮችን በነፍጥ ለመፍታት መሞከር ችግሩን ያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል።

“ሰላም ስናገኛት ርካሽ ስናጣት ደግሞ ውድ ናት” የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የሀገርን እድገትና የዜጎችን በሰላም ወጥቶ መግባት ለማረጋገጥ ሁሉም ለሰላም ቀናዒ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

በመሆኑም ዛሬ የተሰየመውን የሰላም ቀንን ጨምሮ 365ቱንም ቀናት ስለሰላም መነጋገርና የሰላም አሴቶችን ማዳበር ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለሰላም የትኛውም ዋጋ ሊከፈል እንደሚገባ የተናገሩት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፤ ሰላም ከደፈረሰ በኋላ ነፍጥ መማዘዙ ችግሮችን ማባባስ እንጂ አንዳችም መፍትሄ እንደማያመጣ ይናገራሉ።

የነፍጥ መንገድ የኢትዮጵያን መከራ ሲያከብድ ባለፉት 50 ዓመታት በተጨባጭ አይተናል የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የህዝብን ችግርና መከራ እያከበዱ ያሉ ኃይሎች ነፍጣቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም ዋነኛ ዓላማም የግጭት አዙሪት አብቅቶ ችግሮችን በውይይት በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል መሆኑን ገልጸዋል። 

በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ታጣቂዎችን ጨምሮ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ጦረኞች ነፍጥ በማውረድ ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

በነፍጥ አንጋቢዎች ምክንያት የህዝብ መከራና ሰቆቃ እየተባባሰ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፤ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ የሰላም መንገድ በመሆኑ በ215 ዓ.ም ታጥቀው ውጊያ ላይ ያሉ ሁሉ ነፍጣቸውን አውርደው ወደ ውይይትና ምክክር እንዲመጡ ጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም