የሰላም ቀን በተለያዩ ከተሞች እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ቀን በተለያዩ ከተሞች እየተከበረ ነው
ሠመራ /ሀረር/አዳማ ፤ ጳጉሜን 3/2014(ኢዜአ) የሰላም ቀን በተለያዩ መርሃ-ግብር በአፋር ና በሀረሪ ክልልሎች እየተከበረ ነው።
በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከተከበረው መርሃ-ግብር መካከል የሰላም ተምሳሌትና መልካም ምኞት መግለጫ የሆነ የሰላም ምሰሶ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ተመርቆ የተከፈተው ይገኝበታል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የፓናል ውይይትም ተጀምሯል የሰላም ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በተለያየ ዝግጅት እየተከበረ ይገኛል።
በተመሳሳይ በሀረሪ ክልል የሰላም ቀን እየተከበረ ሲሆን በፕሮግራሙም የክልሉ ርእሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ቀኑ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች በከተማው አየተከበረ ይገኛል።
በከተማውም የሰላም ተምሳሌት፣የአንድነትና የመልካም ምኞት መግለጫ የሆነ “የሰላም ፖል” በርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተመርቆ ተከፍቷል።
በተጨማሪም የክልሉ ከፍተኛ አመራር አካላትና ነዋሪዎች፣የመንግስት ሰራተኞች፣የጸጥታ አካላት፣የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይትም በመካሄድ ላይ ነው።
በተመሳሳይ ዜና በአዳማ ከተማ የሰላም ቀንን በማስመልከት የተለያዩ የጸጥታ አካላትን ወታደራዊ ሰልፍ በማድረግ አክብረዋል።
የጸጥታ አካላት ባቀረቡት ወታደራዊ ሰልፍና ባስተላለፉት መልእክት “ተቀናጅተን በአንድነት የሀገራችንና የአካባቢያችን ሰላም እናስጠብቃለን ፣መከላከያ ሠራዊት ለህይወቱ ሳይሳሳ የኢትዮጵያ ዳርድንበሯንና እድነት በማስጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ያደርገ ላለው ትጋት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
የሰላም ቀን እየተከበረ ያለው ከከተማው ሁሉም ቀበሌዎች የተቀጣጡ የሚሊሻ፣ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አከላት በተሳተፉበት ነው።