ለሠራዊቱ ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለሠራዊቱ ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
ደባርቅ እና ሰቆጣ (ኢዜአ) ጳጉሜን 2/2014--ለመከላከያ ሰራዊት ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእርድ እንስሳትና የስንቅ ድጋፍ ተደረገ።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሎጀስቲክስ አስተባባሪዋ ወይዘሮ ደብረወርቅ ይግዛው ዛሬ ድጋፉን ሲረከቡ እንዳሉት፣ ህወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ትቶ ወደጦርነት ገብቷል።
ለመከላከያ ሰራዊቱ የአማራ ባለሃብቶችና የምዕራብ ጎጃም ዞን ህዝብ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የእርድ እንስሳትና የስንቅ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ድጋፉ 104 ሰንጋ በሬ፣ 638 በግና ፍየሎች እንዲሁም የተዘጋጀ በሶ፣ ቆሎና ስኳር መረከባቸውን ጠቁመው፣ ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በመከላከያ ሠራዊት የሎጀስቲክስ ኮሚቴ አባል ኮሎኔል ሽመልስ ብርሃኑ በበኩላቸው "ድጋፉ የሠራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን የውጊያ ሞራል በማነሳሳት ለድል የሚያበቃ ነው" ብለዋል።
የህብረተሰቡ ድጋፍ ሠራዊቱ ግዳጁን በተሻለ እንዲወጣ ስለሚያደርግ በቀጣይም የደጀንነት ተግባሩን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
"ሀገር ስትደፈር ቆሞ የሚያይ የለም" ያሉት ደግሞ ድጋፉን ያስረከቡት የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ ናቸው።
በእዚህም የእርድ እንስሳትና ስንቅ ማስረከባቸውን የገለጹት አቶ ዘመኑ፣ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተያያዘ ዜና ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበሬ ሠንጋና የስንቅ ድጋፍ መረከባቸውን የገለጹት ደግሞ የሎጀስቲክ ኮሚቴ አባል ብርጋዴል ጀነራል ይታያል ገላው ናቸው።
"ድጋፉ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደጎን ብሎ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በግንባር እየተዋደቀ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀን እንዳለው ማሳያ ነው" ብለዋል።
ከአማራ ባለሃብቶች፣ ከሰቆጣ ከተማ ነጋዴዎች እና ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር 80 ሰንጋ፣ 270 የበግና ፍየል ሙክት እንዲሁም 160 ኩንታል በሶ፣ ስኳርና ቴምር በድጋፉ መረከባቸውንም ገልጸዋል።
የሰቆጣ ከተማ ንግድና ማህበራት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ መሰለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ምክር ቤቱ ከአባላት ባሰባሰበው ገንዘብ 20 ሠንጋ በሬዎችን፣ ጁስና ስንቅ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
"ህወሓትን ወረራ ለመከላከል ጠላትን በግንባር እየተፋለመ ላለው ሠራዊት የአዊ ህዝብ የደጀንነት ሚናውን ይወጣል" ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ የኔሰው ናቸው።
እንደ ሀገር የተደቀነው ፈተና በድልለማጠናቀቅ ህዝቡ በስንቅ አቅርቦት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የዞኑ ሚሊሻዎች ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ተሰልፈው አጋርነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል።