ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሚገባ በማስተዋወቅ የመላ አፍሪካውያን እሴት እንዲሆን መስራት አለብን-መጋቢ ሃዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ጳጉሜን 2/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሚገባ በማስተዋወቅ የመላ አፍሪካውያን እሴት እንዲሆን መስራት እንደሚገባ የስነ-ፈለክ ተመራማሪው መጋቢ ሃዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ተናገሩ።

በዓለም ላይ የተለየ የዘመን አቆጣጠርና ፊደል ካሏቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን ከሌሎች በተለየ አዲስ ዓመታቸውን በወርሃ መስከረም የሚጀመሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የግሪጎሪያን የዘመን ቀመር ከሚጠቀሙ አገራት ጋር ከመስከረም እስከ ጥር ወራት በሰባት፤ እንዲሁም ከየካቲት እስከ ነሃሴ በስምንት ዓመት ይለያያል፡፡

የዘመን መባቻው መስከረም የሆነበት ስነ-ፈለካዊና ተፈጥሯዊ ምክንያት እንዳለው መጋቢ ሃዲስ ዶክተር ሮዳስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ፀሀይ ምድር ወገብ ላይ በምትሆንበት ወቅት ቀኑና ሌሊቱ እኩል ከሚሆንባቸው ሁለት ወራት መካከል መስከረም አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ መስከረም የቃሉ ትርጉም "የክረምት መምሻ ወይም  ክረምት የሚያበቃበትና መፀው የሚብትበት" ማለት መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያን የዘመን ቀመር በሚገባ በማስተዋወቅ የመላ የአፍሪካውያን እሴት ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ቢገባም በዚህ በኩል በሚፈለገው ደረጃ ተሰርቷል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው የተናገሩት።

የዘመን ቀመሩ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ተማሪዎች ከልጅነታቸው አንስቶ እንዲያውቁ አለመደረጉና የጥንት ኢትዮጵያውያን ስለፈለክ ሳይንስ በትምህርት ቤት ባለመሰጠቱ ትውልዱ ከዘመን ቀመሩ ጋራ አልተዋወቀም ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃንና የሚመለከታቸው አካላት የዘመን አቆጣጠሩን በማስተዋወቅ በኩል የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የዘመን አቆጣጠሩን በስርዓተ ትምህርት በማካተትና በሚገባ በማስተዋወቅ መላ አፍሪካዊያን እንዲገለገሉበት ጭምር መስራት እንደሚገባም ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም