ጽህፈት ቤቱ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ነቀምቴ፤ ጳጉሜን 2/2014 (ኢዜአ)፤ የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ጽህፈት ቤቱ ድጋፉን ያደረገው ትናንት ተከብሮ የዋለውን የበጎ ፈቃድ ቀንን ምክንያት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ትግሥት ቦጄ በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ድጋፉ ’’ዛሬ ሕፃናትን በመርዳት የነገ ተስፋን እንገንባ’’ በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

ድጋፉ ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ለ2 ሺህ 446 ተማሪዎች መደረጉን አመልክተው፤

በድጋፉም ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ብር ዋጋ ያላቸው የመማሪያ ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ለተማሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።ድጋፉን የከተማው ነዋሪዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ መንግሥታዊ ልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፣የከተማ አስተዳደሩ የሴክተር መሥሪያ ቤቶና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማድረጋቸውን አስታውቀው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የከተማ አስተዳሩ ከንቲባ አቶ ቶሌራ ረጋሣ በበኩላቸው ድጋፉን ለደረጉት የተለያዩ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍ የነገ ተስፋ የሆኑ ሕፃናት ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲማሩ እና በሀገር ዕድገት ውስጥ ያላቸው ሚና እንዲያድግ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እርዳታው ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል የጨለለቂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ሽብሬ ተስፋ የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ትምህርቷን ለመቀጠል ስጋት ሆኖባት እንደነበር ተናግራለች።

የትምህርት መሳሪያዎችን በድጋፍ በማግኘቷ በጣም ደስተኛ መሆኗን ገልጻ፣ ይህንን ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አመስግናለች፡፡

የቢፍቱ ነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ራሄል ተስፋዬ በበኩሏ በተደረገላት ድጋፍ መደሰቷን ገልፃ፤ ድጋፍን ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርባለች፡፡

ድጋፉ ትርጉም ያለው እና በትምህርቱ እንዲበረታ የሚያደርገው መሆኑን የተናገረው ደግሞ የቢፍቱ ነቀምቴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ናኦል ታደሰ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም