ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የትብብር እንጂ የንትርክ መንስኤ ሊሆን አይገባም- የሱዳን ምሁራን

አዲስ አበባ ጳጉሜን 2/2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የትብብር እንጂ የንትርክ መንስኤ ሊሆን እንደማይገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሱዳናዊያን ምሁራን ተናገሩ።

በኢትዮጵያዊያን የጋራ ትብብርና ጥረት እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሃይል ማመንጫነቱ ባለፈ ዋነኛ የቱሪስቶች መዳረሻ የሚሆን ነው።

የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ1 ሺህ 700 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚንጣለለው ሐይቅ የዓሳ ምርትም የአካባቢው ውበትም ሆኖ የሚታይ ይሆናል።

በሃይቁ ላይ የሚፈጠሩት ከ70 ያላነሱ ደሴቶች የቱሪስቶች መዳረሻ ሲሆኑ አካባቢው የበርካታ አእዋፋት፣ እንስሳትና የእፅዋት ማእከል ጭምር የሚሆን ነው።

የግድቡ መገንባት ከመንም በላይ በጨለማ ለሚኖሩ ብርሃን እንዲሆም በሃይል እጥረት በሙሉ አቅማቸው ማምረት ላልቻሉ ኢንዱስትሪዎች የሃይል አማራጭ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገር አልፎ ለአህጉራዊ የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ መሰረት እንደሚሆን ይታመናል።

በሱዳን ካርቱም ተቀማጭነቱን ያደረገው የአፍሪካ የአስተዳደር፣ ሰላምና ሽግግር ጥናት ማዕከል ዋና ፀሐፊ ዶክተር ማህሙድ ዘይንላብዲን፤ እንደሚሉትም ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ ተርጉም የሚሰጠው ነው።

ዶክተር ማህሙድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳን ህዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የጠቀሱት።

በግብርናው ዘረፍ ሱዳናዊያን በዓመት ሶስት ወቅቶች እንመርቱ፤በሱዳን ከተሞች የሚድርሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመቀነስና በዋነኝነት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኅይል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑን ያብራራሉ።

ግድቡ ለጎረቤትና እህትማማች አገሮች ሁለንተናዊ ትስስር መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ማህሙድ፤ የዓባይ ውሃ የተፋሰሱ አገራት የውጥረት ምክንያት ሳይሆን የልማትና የትብብር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አገራቱ በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው ከተንቀሳቀሱና የጋራ ተቋማዊ አደረጃጀት ከፈጠሩ የመልማት እድላቸው ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል።

የናይል ኢኒሸቲቭና መሰል ተቋማት አገራቱን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ ሁሉም ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓባይ ጉዳይ አዋጩ መፍትሔው ምክንያታዊ፣ ፍትሃዊና ዘላቂነትያለው የውሃ ሀብት አጠቃቅምን መተግበር መሆኑን ገልጸዋል።

የቀድሞ የሱዳን ሪፐብሊክ መስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር ዑስማን አቱም፤ ዓባይ በኢትዮጵያ በጥልቅ ሸለቆዎች፣ በሱዳን ደግሞ በሜዳማ ቦታዎች ላይ እየፈሰሰ ሁለቱን አገራት ያስተሳሰረ ስጦታ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ለኤሌከትሪክ ኅይል ማመንጫ፣ ሱዳን ደግሞ ለመስኖ ልማት የመጠቀም ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህን ሀብት በትብብር አልምቶ በጋራ መጠቀም ይቻላል ይላሉ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃን በመያዝ ለሱዳንና ግብጽ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ግድቡ በግብጹ አስዋን ግድብ በየዓመቱ የሚባክንውን ከ4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ከትነት የሚታደግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዓባይን ውሃ በአሌክትሪክና በሌሎች አገልግሎቶች በመተባበር በስርዓት ማልማት ከተቻለ ለሶስቱም አገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚበቃ መሆኑን ዶክተር ዑስማን አስረድተዋል።

ምናልባት በትብብር መራመድ ከተቻለ በ2040 ምስራቃዊ ናይል ምጣኔ ሀብታዊ ዞንን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሶስቱ አገራት ለሌላው ዓለም የሚተርፉበት ወርቃማ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህም ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ምጣኔ ሀብታዊ ግንባታ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ፖለቲካዊ መልክ እየተሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃን ለኤሌክትሪክ ኅይል ማመንጫነት የሚጠቀም እንጂ የዓባይን ውሃ የሚያስቆም ግድብ ባለመሆኑ፤ አገራት ከተባበሩ ማንም ሳይጎዳ ይልቁኑም ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

ሶስቱም አገራት ከስምምነት ለመድረስ መፍትሄው ውጫዊ ሶስተኛ ወገን መሻት ሳይሆን የመፍትሄ አካል ቁርጠኛ ሆኖ እርስ በርስ መነጋገርና ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም