ቀጥታ፡

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሃላፊነታቸውን ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው-አምባሳደር ሂሩት ዘመነ

ጳጉሜን 2 /2014 (ኢዜአ) የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሃላፊነታቸውን ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ተናገሩ፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የተሰጣቸውን አለም አቀፍ ሃላፊነት እየተወጡ አይደለም ሲሉ አምባሳደሯ መግለጻቸውን ሄልዝ ፖሊሲዎች የተባለ ድረ-ገጽ አስነብቧል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰጧቸው አስተያየቶች ከሙያ ስነ-ምግባር ያፈነገጡ፣ስልጣናቸውን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ መሆኑን የሚያመለክቱ ብሎም ተንኳሽ መሆናቸውን አምባሳደሯ አንስተዋል።

አምባሳደር ሂሩት አክለውም “ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር የሚመለከቱበት መንገድ ከሙያው በእጅጉ የራቀ ነው” ብለውታል፡፡

“የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመሰለ ግዙፍ ተቋም ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት የያዘ ሰው የአለም ጤና ጉዳይ ሊያሳስበው ሲገባ ስለሆነ ቦታ ብቻ በማውራት መጠመዱ አሳፋሪና ለያዘው ሃላፊነት የማይመጥን ነው” ብለውታል።

“የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር” የሚል ትልቅ ሃላፊነት በመያዝ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የሚያሳፍርና ስልጣንን ለእኩይ አላማ የመጠቀም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም