ህወሃት የራሱን ዕድሜ ለማራዘም በሀሰት ትርክቶች የትግራይን ወጣት እያስፈጀ ነው--ምርኮኛ የህወሓት ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ህወሃት የራሱን ዕድሜ ለማራዘም በሀሰት ትርክቶች የትግራይን ወጣት እያስፈጀ ነው--ምርኮኛ የህወሓት ታጣቂዎች
ደባርቅ ጳጉሜን 1/2014 (ኢዜአ) ''አሸባሪው ህወሓት የራሱን ዕድሜ ለማራዘም በማሰብ በጠላት ተወረሀል፤ የዘር ማጥፋት ሊፈፀምብህ ነው በሚሉ የሀሰት ትርክቶች የትግራይን ወጣት እያስፈጀ ነው'' ሲሉ በደባርቅ ግንባር የተማረኩ የህወሓት ታጣቂዎች ተናገሩ።
ምርኮኞቹ በደባርቅ ግንባር አሸባሪ ቡድኑ ለ3ኛ ጊዜ በጀመረው ጦርነት ታዳጊ ህጻናትን ሳይቀር ከወላጆቻቸው በመንጠቅ ለጦርነት እየማገደ መሆኑንም ገልጸዋል።
በደባርቅ ግንባር ከተማረኩት የህወሓት ታጣቂዎች መካከል ወጣት ሰመረ ፀጋዬ እንዳለው፣ ከአዲግራት ደብረዳሞ አካባቢ "ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው" በሚል በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ተገዶ ወደውጊያ መግባቱን ገልጿል።
ህወሓት "በጠላት ተከበሀል" በሚል የሃሰት ትርክት የትግራይን ወጣት ለጦርነት በመማገድ እያስጨረሰው መሆኑንም ተናግሯል።
ወጣቱ በደባርቅ ግንባር ደፈጣ ውጊያ ላይ ሳሉ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ምት ከሞት ከተረፉ ሌሎች ጓደኞቹ ጋር ቆስሎ መማረኩን ገልጿል።
ምርኮኛው የህወሓት የስልጣን ጥመኞች በጦርነቱ እጃችሁን እንዳትሰጡ ይገሏችኋል በሚል ይሰብኳቸው እንደነበረም ነው የገለጸው።
"ከተማረኩ በኋላ የገጠመኝ ከእዚህ በተቃራኒው ነው" ያለው ወጣቱ፣ ህዝቡና መከላከያ ሠራዊት ከወደቀበት ገደል በማውጣት ህክምናና እንክብካቤ እንዲያገኝ ማደረጉን ገልጿል።
በርኽ ይበይን የተባለ ሌላው ምርኮኛ በበኩሉ ህወሓት ዕድሜውን ለማራዘም የትግራይን ህዝብ "የዘር ማጥፋት ታውጆብሃል፤ ታግለን ህዝቡን እናድን'' በሚል ከመምህርነት ሙያው አስገድዶ በማስውጣት ወደ ግንባር እንዳስገባው ተናግሯል።
"ጓደኛዬ በጦርነቱ ግራ እጁ ሲቆስል ራሳችንን እናጥፋ ሲለኝ ሀሳቡን በመቃወም እጄን ለመከላከያ ሰራዊት ሰጥቻለሁ'' ሲል ተናግሯል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተማረከበት ቀን ጀምሮ ህክምናና እንክብካቤ እያገኘ መሆኑንም አስተድቷል።
መንግስት ባቀረበው የሰላም አማራጭ በግንባር የተሰለፈው የትግራይ ወጣትም ሆነ ህዝቡ ደስተኛ ቢሆንም ህወሓት የሰላም አማራጩን ወደጎን ብሎ ህጻናትና ወጣቶችን በጦርነት እየማገደ መሆኑን ተናግሯል።
"የህወሓት አመራሮች ለትግራይ ህዝብ የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ የሚከፈለውን ከባድ ዋጋ ሁሉ ከፍለው ህዝቡንና ወጣቱን ዓላማ በሌለው ጦርነት አያስፈጁትም ነበር" ብሏል።
''በጦርነት መጠፋፋት እንጂ የሚገኝ ትርፍ የለም'' ያለው ምርኮኛው በጦርነቱ ህፃናት ጭምር እያለቁ ነው፣ ትውልዱም ከባድ ዋጋ እየከፈለ በመሆኑ ቡድኑ ጦርነቱን አቁሞ ወደሰላም እንዲመጣ ጠይቋል።
በደባርቅ ግንባር የተማረከው ሌላው ወጣት ደሳለኝ አዲስ በበኩሉ ከወንድሙ ጋር በበርሃ ፍየል እያረባ በነበረበት ወቅት ወደግንባር ተገዶ እንዲገባ መደረጉን አስታውሷል።
አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ በእርዳታ የሚላክን ስንዴ ሳይቀር ለግል ጥቅሙ እየዋለ መሆኑንም ወጣቱ አስረድቷል።
ይባስ ብሎም በየጊዜው 500 መቶ ብር እንዲያዋጣና ለጉስቁልና እንዲዳረግ እያደረገ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር በሽብር ቡድኑ ላይ ጫና እንዲያሳድር ጠይቋል።
ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ እንደሆነችና "የትግራይን ህዝብ ነፃ እናወጣለን'' በሚል ፕሮፖጋንዳ ተገዳ በአንድ ወር ስልጠና ወደውጊያ እንደገባች የገለጸችው ሌላኛዋ ምርኮኛ ተማሪ አፀደ ወልደሚካኤል ናት።
"ውጊያ እንደተጀመረ አምስት ሆነን እጃችንን ሰጠን" ያለቸው ምርኮኛዋ፣ "እንደተማረክን የገጠመን እንደተነገን ሳይሆን ባልጠበቅነው ሁኔታ ምግብና ውሃ በማቅረብ ተንከባክበውናል" ስትልም ምስክርነቷን ገልጻለች።
ህወሓት በተደጋጋሚ በለኮሰው ጦርነት የትግራይ ወጣትና ህዝብ እያለቀ በመሆኑ የአሸባሪው ቡድን አመራሮች የሰላም አማራጭን ቆም ብለው በማሰብ ህዝቡን ከዕልቂት እንዲታደጉት ጠይቃለች።