ቀጥታ፡

ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን የደጀንነት ድጋፋችንን እናጠናክራለን -- ወጣቶች

ደባርቅ ፤ ጳጉሜን 1/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህውሃት ቡድን የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን ትቶ የፈጸመው ዳግም ወረራ እስኪቀለበስ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሚያደርጉትን ደጀንነት እንደሚያጠናክሩ የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

ቡድኑ ባለፈው ዓመት በሰሜን ጎንደር ዞን ጭና ቀበሌ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ መጨፍጠፉ ይታወሳል።

በከተማው የተቋቋመው ''የኢትዮጵያ ታሸንፋለች'' የበጎ አድራጎት ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሰሎሞን ኪዴ አሸባሪው ቡድን በአካባቢው ወረራ በፈጸመበት ወቅት ከፍተኛ የሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ለኢዜአ ተናግሯል።

ወጣቱን ጨምሮ የደባርቅና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ ቡድኑ በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ አሻፈረኝ በማለት ዳግም የለኮሰው ጦርነት በድል እንዲቋጭ የደጀንነት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጿል።

በተለይም በግንባር ለሚገኘው ሰራዊት ምግብ በማዘጋጀት ግንባር ድረስ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሷል።

ቡድኑ የሚያሰራጨውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ማጋለጥ፣ ኬላዎችን ነቅቶ የመጠበቅ፣ ሰርጎ ገቦችን ተከታትሎ የመያዝና የአካባቢውን ሰላም በንቃት የመጠበቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።  

አሸባሪው ቡድን የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን ትቶ የለኮሰው ጦርነት በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።   

አሸባሪው ቡድን ለግል ጥቅሙና ስልጣኑን ለማራዘም ቆሜልሃለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብ ታዳጊዎች ያለእድሜያቸው በለኮሰው ጦርነት ከፊት አሰልፎ ለሞት መማገዱ እንዳሳዘነው የገለጸው የማህበሩ አባል ወጣት ያሬድ ግርማ ነው።

ከደጀንነት ተግባሩ ባለፈ አሸባሪ ቡድኑ የሚነዛውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማምከን ህዝቡ እውነታውን እንዲረዳ እየሰራ መሆኑን የሚናገረው የሚናገረው ደግሞ ወጣት ዳንኤል ዘመን ነው።   

ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ግንባር ድረስ በመሄድ ምግብ በማቅረብ፣ ሌሎች የደጀንነት ተግባርን እየተወጣ መሆኑን አመልክቷል።  

ትግሉ ፍፃሜ እስኪያገኝ ድረስ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ጸጥታ አካላት እያደረገ ያለውን የደጀንነት እንደሚያጠናክር ጠቅሷል።

ባለፈው አመት የሽብር ቡድኑ በጭና ቀበሌ በፈጸመው ወረራ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ላይ የፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ አንደኛ አመት ዝክረ  ሰማእታት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ መዋሉን  ኢዜአ መዘገቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም