ቀጥታ፡

በዲጂታል ሚዲያ የኢትዮጵያን ፍላጎትና አቋም የሚያንጸባርቁ አጀንዳዎች በስፋት ተደራሽ እየሆኑ ነው- የማህበራዊ ሚዲያ አንቂው ሱሌማን አብደላ

ጷጉሜን 1/2014/ኢዜአ/ በዲጂታል ሚዲያ የኢትዮጵያን ፍላጎትና አቋም የሚያንጸባርቁ አጀንዳዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የማህበራዊ ሚዲያ አንቂና የፖለቲካ ተሟጋቹ ሱሌማን አብደላ ገለጸ።

የዲጂታል ዲፕሎማሲው ተቋማዊ አሰራር ተበጅቶለት በተደራጀ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባውም ተናግሯል።

የማህበራዊ ሚዲያ አንቂና የፖለቲካ ተሟጋቹ ሱሌማን አብደላ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ አሸባሪው ሕወሓት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል ዳግም ጦርነት ስለመጀመሩ ይናገራል።

በአንድ በኩል ጦርነት ከፍቶ በሌላ በኩል ደግሞ “የትግራይ ክልል ተጠቃ፤ ተከበናል" እና ሌሎችም የማደናገሪያ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን ጠቅሷል።

በመሆኑም የአሸባሪ ቡድኑን የሀሰት ዘመቻ ለማጋለጥ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ኢትዮጵያን የተመለከቱ መልዕክቶችን በመቅረጽ ለመላው ዓለም ተደራሽ የማድረግ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።

በተለይም በትዊተር ዘመቻ አሸባሪው ህወሃት ጦርነት መጀመሩን፣ የትግራይን ህጻናት እያስፈጀ መሆኑን እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታና እርምጃ እንዲወሰድበት የሚጠይቁ አጀንዳዎች እየተንሸራሸሩ መሆኑን ሱሌማን አብራርቷል።

በዲጂታል ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያውያንን ፍላጎትና የመንግስትን አቋም የሚያንጸባርቁ መልዕክቶች ከባለፉት ጊዜያት በተሻለ መልኩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እየሆነ ነውም ብሏል።

አሸባሪው ሕወሓት ከከፈተው ዳግም ጦርነት ጋር በተያያዘ እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥና በተቀናጀ መልኩ የኢትዮጵያን ጥቅም የማስጠበቅ ስራዎች በተደራጀ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን አመልክቷል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚከናወኑ ዘመቻዎች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ የኢትዮጵያ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ተናግሯል።

የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራው ዘለቄታዊ ጥቅም እንዲያስገኝ ተቋማዊ አሰራር ሊበጅለት እንደሚገባም ነው የማህበራዊ ሚዲያ አንቂው የገለጸው።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በሚገኙባቸው ሀገራት መገናኛ ብዙሃን የሀገራቸውን አቋም ማስረዳት  እንዳለባቸውም እንዲሁ።

የመንግስት ወቅታዊ መረጃ አሰጣጥ የሚበረታታ ነው ያለው ሱሌማን፤ ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው መሆኑንም አመልክቷል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው የተከፈተባትን ዘርፈ ብዙ ጦርነት በጋራ እንዲመክቱም ሱሌማን ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም