በብሪታንያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለየሀገራቱ ባለስልጣናት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ገለጻ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በብሪታንያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለየሀገራቱ ባለስልጣናት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ገለጻ አደረጉ
ጷጉሜን 1 ቀን 2014(ኢዜአ) በብሪታንያ እና በኮሪያ ሪፐብሊክ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ለየሀገራቱ ባለስልጣናት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በብሪታንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ለብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
አምባሳደሩ አሸባሪው ሕወሓት በአፍሪካ ህብረት ሊመራ የታሰበውን የሰላም ሂደት ውድቅ ማድረጉን እንዲሁም በአማራ እና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱን አብራርተዋል።
መንግስት በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀው እንግሊዝ ይህንን ሂደት ለመደገፍ ያደረገችውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ለብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ አሸባሪ ቡድኑን ከአማራ ክልል እንዲወጣ ለሰጡት ማሳሰቢያ አመስግነው ሕወሃት ለየትኛውም አይነት የሰላም ሂደት ዝግጁ አለመሆኑን አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ የሕወሓትን ውል የለሽ እና ለብዙ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ያለውን ጦርነት ማውገዝ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ ችግሮችን ለመቅረፍ አማራጮችን ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
በተመሳሳይ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለኮሪያ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ቢሮ ዳይሬክተር ኪም ጃንግ ሀዩን ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል የተኩስ ማቆም እርምጃ መውሰዱን በገለጸቸው አመልክተዋል።
በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ለሚካሄደውም የሰላም አማራጭ ኮሚቴ እስከማቋቋም መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም የሽብር ቡድኑ ሰላማዊ አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጦርነት ጀምሯል ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጦርነቱ ቀስቃሽ መሆኑን በመገንዘብ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጣ ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡