ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም አገርን ማሻገር የሚያስችሉ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች

268

ነሃሴ 30 ቀን 2014(ኢዜአ)  ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም አገርን ማሻገር የሚያስችሉ ድሎችን እንዳስመዘገበች ተጠቆመ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ፈተና፣ድልና ተስፋ" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እንዲሁም የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም ያለፈችበትን የሰላም፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በዓመቱ ኢትዮጵያ በተለይ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡

የአሸባሪው ህወሃት ወረራን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ መደፍረሶችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ነገር ግን በጸጥታ ኃይሉና በዜጎች የተቀናጀ ተሳትፎ ያጋጠሙ የሰላም ፈተናዎችን መመከት መቻሉን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ በጸጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡

በሪፎርሙ የጸጥታ ተቋማት ኢትዮጵያን በሚመጥን አግባብ እንዲደራጁ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም በጸጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በውጤታማነት ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚሰራም ነው ያብራሩት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው በዓመቱ በፖለቲካው መስክ ዓበይት ድሎች መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡

በዓመቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ የመንግስት ምስረታ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወስጥ አዲስ ምእራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካታች የሆነው የፖለቲካ መንገድ መንግስት በፓርቲዎች ውስጥ ያለውን አቅም ለህዝብ ጥቅም እንዲያውል እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

ህዝብን በሚያገለግሉ አካላት መካካል የውይይት ባህልን በማጎልበት ዜጎችን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ  ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋምም በዓመቱ በፖለቲካው መስክ ከተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ በዓመቱ የኢኮኖሚው መስክ በዓለም አቀፍና አገራዊ ምክንያቶች ከፍተኛውን ፈተና እንዳስተናገደ አስታውሰዋል፡፡

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነትን በዚህ ረገድ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡    

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ በበርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የወጪ ንግድን ለአብነት ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በሸቀጦችና አገልግሎት ወጪ ንግድ እንዲሁም ከሬሚታንስና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ 22 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በሂደቱም ለ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በዓመቱ በአጠቃላይ ከመኸርና ከበጋ መስኖ ልማት 90 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ 26 ሚሊዮን ኩንታሉ በበጋ መስኖ የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠልና ፈተናዎችን ደግሞ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወጣቶች ኢትዮጵያን እያጋጠሟት ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በሚገባ በመገንዘብ የመፍትሔው አካል መሆን እንዳለባቸው ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም