የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ የሆኑ የባህል አልባሳትን በመልበስ ለዓለም ልናስተዋውቅ ይገባል- የባህል አልባሳት ሸማቾች እና ነጋዴዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ የሆኑ የባህል አልባሳትን በመልበስ ለዓለም ልናስተዋውቅ ይገባል- የባህል አልባሳት ሸማቾች እና ነጋዴዎች

ነሃሴ 30/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ የሆኑ የባህል አልባሳትን በመልበስ ለዓለም በማስተዋወቅ ዋነኛ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህል አልባሳት ሸማቾች እና ነጋዴዎች ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያውያን አዲስ ተስፋና ራዕይ ሰንቀው የ2015 የዘመን መለወጫን ሊቀበሉ ጥቂት ቀናት ቀርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ፣ አዲስ እቅድ፣ አዲስ የስኬት መንገድን ከመተለም ባሻገር በአዲስ ዓመት በአዲስ ልብስ መድመቅንም ያውቁበታል።
በዓሉንም እንደየባህላቸው በየአካባቢያቸው የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን በመልበስ ዘመድ ወዳጅ አብረው ያሳልፋሉ።
ለዘንድሮው አዲስ ዓመትም እንደየአቅማቸው በአዲስ ልብስ ደምቆ በዓሉን ለማክበር የባህል አልባሳት ገበያው ሞቅ ደመቅ ብሏል።
ኢዜአ በአዲስ አበባው የሽሮሜዳ የባህል አልባሳት ገበያ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች የባህል አልባሳት ገበያው ሞቅ እያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሸማቾች መካከል ወይዘሮ መድኃኒት ቦጋለ ናወጣት እስራኤል ጌታሁን ለገበያ የቀረቡ የባህል አልባሳት በበዓል ወቅትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ የሚለበሱ ሆነው መዘጋጀታቸው ለተጠቃሚዎች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የባህል አልባሳትን ከበዓላት ውጭ በመደበኛ ጊዜም በመልበስ ኢትዮጵያንና ባህሏን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው ያብራሩት።
አልባሳቱ በጥሩ ሁኔታ ቢዘጋጁም የዋጋ ጭማሪ መኖሩን በመጠቆም ወጣቶች እንደየአቅማቸው የባሀል አልባሳትን በማዘውተር ባህላቸውን ሊያስተዋውቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የባህል አልባሳትን የሚሸጡ ነጋዴዎች በበኩላቸው መጪውን የ2015 የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ አልባሳትን ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የኢትዮጵያን የባህል አልባሳት ለመላው ዓለም እያስተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ለውጭ ዜጎች ጭምር አልባሳቱን እየሸጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህል አልባሳትን የመልበስ ልምድ እያደገ መምጣቱ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚም ፋይዳው የላቀ በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም እንዲሁ።