የናይልና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ተቋማዊ ስራና የትብብር ማዕቀፎች መጠናከር አለባቸው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የናይልና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ተቋማዊ ስራና የትብብር ማዕቀፎች መጠናከር አለባቸው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ነሐሴ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የናይልና ሌሎች የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ምክንያታዊና ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ተቋማዊ ስራና የትብብር ማዕቀፎች መጠናከር እንዳለባቸው ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው በናይል ወንዝ ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የተፋሰሱ ሀገራት ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
አቶ ደመቀ አክለውም የዛሬውን መሰል የጋራ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ይጠቅማሉ ነው ያሉት።
በቀጣናው ያለውን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነት ከተጠቀምነው በቂ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳት እንደሌለውና የውሃ ፍሰት ተፅዕኖ እንደማያደርስ በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚከሰቱ የጎርፍ መጥለቅለቆች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሱ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም በውሃ ሀብቶች ላይ ያለንን አጠቃቀም ለማስተካከልና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በጋራ ለመስራት እንደሚያስገድድም ተናግረዋል።
ተመራማሪዎች በሀገራት ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ላይ ትክክለኛ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ፣ ሚዲያዎች ደግሞ ሁሉን አቀፍ ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን ድምፅ መሆን እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የተፋሰሱ ሀገራትና የቀጣናው የዘርፉ ተቋማት ተወካዮች፣ በተፋሰሱ ሀገራት የሚገኙ ከሰባት በላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና የናይል ጉዳይ ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባኤ በናይል ውሃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።