አሸባሪው ህወሓት የሰላም አማራጭን ረግጦ ጦርነት መክፈቱ በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ቆሞ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ነው- ምርኮኞች

ነሐሴ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ረግጦ ዳግም ጦርነት መክፈቱ በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ቆሞ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ነው ሲሉ በተለያዩ ግንባሮች እጃቸውን ለጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰጡ ምርኮኞች አጋለጡ፡፡

ምርኮኞቹ እንደተናገሩትም የትግራይን ህጻናት ሳይቀር ወደ ጦር ግንባር እየማገደ የሚገኘው አሸባሪው ህወሃት በሃሰተኛ ትርክት የትግራይን ወጣት ራሱ ወደለኮሰው ጦርነት እየማገደ ክልሉን ትውልድ አልባ የማድረግ እኩይ አላማውን ገፍቶበታል።

ይህም ተግባሩ የሽብር ቡድኑን የባንዳነት ትክክለኛ ባህሪ በተጨባጭ እያረጋገጠ መሆኑንም ነው ምርኮኞቹ የተናገሩት።

ምርኮኞቹ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በትግራይ ህዝብና ህፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ስቃይና እንግልት በመቃወም በፕሮፖጋንዳ ተታለው ከገቡበት ጦርነት በመውጣት ለጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እጃቸውን መስጠታቸውን ገልፀዋል፡፡

የሰላም አማራጭ በሰፊው ቀርቦለት ጦርነትን መርጦ ህጻናትን ሳይቀር ወደ ጦርነት እየማገደ ያለው የሽብር ቡድኑ ህወሃት የራሱን የስልጣን ላይ ቆይታ ለማራዘም ትግራይ ላይ ምንም አይነት ጥፋት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይመለስ ምርኮኞቹ አረጋግጠዋል።

"የትግራይ ከፍታ የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ነው" በሚል ቀቢፀ ተስፋ በመነሳሳት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ህዝቦቿን ለመበተን ዳግም ጦርነት ቢከፍትም አላማ ቢስ ለሆነው የሽብር ቡድኑ አላማ መሰለፍ ከንቱ በመሆኑ እጃቸውን ለመስጠት እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል።

በቡድኑ የውሸት ወሬና ፕሮፓጋንዳ ተታለው በመሰለፍ ለፈፀሙት ጥፋት በመፀፀት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለሌሎች የፀጥታ ኃይል ይቅርታ ጠይቀው የህወሃት የሽብር ቡድንን ከንቱ ራስ ወዳድ አላማ ለማስፈፀም የተሰለፉ የትግራይ ወጣቶችም የሚጓዙበት መንገድ ፈጽሞ እንደማያዋጣ በመረዳት ፈጥነው እንዲነቁ ምርኮኞቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ምርኮኞቹ በመከላከያ ሰራዊትና በሌሎች የፀጥታ ሃይሎቻችን ለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና እንክብካቤም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንዳማይገኝ የገለፁት ምርኮኞቹ፤ አሸባሪ ቡድን ለዳግም እልቂት የከፈተውን ወረራ በማውገዝ ወደ ሰላም እንዲመጣ የትግራይ ህዝብ፤ ወጣቶችና ልዩ ኃይል አባላት ጫና መፍጠር እንደሚገባቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም