የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማኅበር ተመሠረተ

ነሐሴ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ ተመሥርቷል።

ማኅበሩን ከዚህ በፊት የተቋቋሙ አምስት ማኅበራት በጋራ እንደመሰረቱት ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደተናገሩት ማኅበሩን ለመመስረት ባለፉት አራት ዓመት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

የማኅበሩ መመስረት ለቡና ልማቱ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው አርሶ አደሩንም ለመደገፍ ድርሻው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ፕሮጀክት በመቅረጽ ትልልቅ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

በአርሶ አደሩ በኩል የሚነሱ የግብአት አቅርቦት ችግርን መፍታት፣ በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ የመድን ተጠቃሚ ማድረግ የማህበሩ ቀጣይ ትኩረቶች ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የማኅበሩ መስራች ጉባኤ እየተካሄደ ሲሆን የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም