በአሜሪካ በአንድ ምሽት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ በአንድ ምሽት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ
ነሐሴ 30 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ።
ዳያስፖራው በተለያዩ መስኮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ቡድን “ሁሉም እጆች ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል።
በመርሐግብሩ ለጨረታ ቀርቦ በ10 ሺህ ዶላር የተሸጠውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የስዕል ስራ ጨምሮ በአጠቃላይ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተሰበስቧል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ዳያስፖራው በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍን ማሳደግ እንደሚገባው ገልጸዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብሩ ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ፣የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።