የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያ ባንኮች በትብብር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያ ባንኮች በትብብር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር ነው
ነሐሴ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያ ባንኮች በትብብር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።
የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ክፍት መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም በጥንቃቄ መመራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
መንግስት ለዓለም አቀፍ ባንኮች ዝግ የነበረውን የባንክ ዘርፍ ክፍት እንደሚያደርግ ሲገልጽ እንደነበር ይታወቃል።
በዚህም ለዘመናት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተትቶ የነበረውን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲዘጋጅ ቆይቷል።
የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ የዘርፉን አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ በመደገፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ይታመናል።
የፋይናንስ ዘርፉን ተወዳዳሪና ቀልጣፋ በማድረግ በቂ የፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ይነገራል።
በዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ ሆኖ መቆየቱ የሀገር ውስጥ ባንኮችን እድገት እንዳቀጨጨው ተናግረዋል።
የውጪ ኢንቨስተሮች በባንክ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ ዓለም አቀፍ ልምድ በሌላቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች ተገድቦ የነበረውን ደካማ ውድድር በማስቀረት አብሮ የመስራት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የባንኩ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ክፍት መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም በጥንቃቄ መመራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ለዓለም ገበያ በሩን ሙሉ በሙሉ ዝግ አድርጎ መቆየቱ በሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል አለመሆኑን አስታውሰው፤ የባንክ አገልግሎቱን ድንገት ለዓለም ገበያ ወለል አድርጎ መክፈትም አደጋ ስለሚኖረው በሚዛኑ ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የባንክ አገልግሎቱን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ የሀገር ውስጥ ባንኮች የውድድር አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መሥራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ውድድር ዓለም አቀፍ ልምዶችን ለመቅሰም ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በውድድሩ የሀገር ውስጥ ባንኮች እንዳይጎዱ በተወሰነ የአክሲዮን ድርሻ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በማድረግ በሂደት የአክሲዮን መጠናቸውን እያሳደጉ የሚሄዱበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
ይህን ማድረግ የሀገር ውስጥ ባንኮችን ባጠረ ጊዜ ወደተሻለ ብርታት ሊያመጣቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።