ቀጥታ፡

የህዝቡ የኋላ ደጀንነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- ዶክተር ድረስ ሳህሉ

ባህርዳር፤ ነሐሴ 29/2014 (ኢዜአ)፡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሚደረገው የህዝቡ የደጀንነት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ አሳሰቡ።

አስተዳደሩ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት  አካሂዷል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዶክተር ድረስ ሳህሉ በመድረኩ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ  በመግፋት ለ3ኛ ጊዜ  ጦርነት በመክፈት በአማራና በአፋር ክልሎች  ወረራ ፈጽሟል።

የሽብር ቡድኑ ዜጎችን ለሞትና ስደት እየዳረገ መሆኑን አመልክተው፤ በንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም አሸባሪው ህወሓት የፈጸመውን ወረራ ለመመከት በግንባር ጠላትን እየተፋለሙ ለሚገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሚደረገው የደጀንነት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የአካባቢውን ሰላም ከሰርጎ ገቦች ተደራጅቶ ከመጠበቅ ባለፈ  የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀልም ጥሪ አቅርበዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የኔሰው መኮንን በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት  ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅዶ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል።

የአሸባሪውን ወረራ ለመመከት በሚደረገው ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ  የውስጥ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

 የከተማው ወጣቶችና ህብረተሰቡ ስንቅ ማዘጋጀትን ጨምሮ እያደረገ ያለውን  የደጀንነት ተግባር  አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብሮ  ኢትዮጵያን ለማፍረስ  የሞት ሽረት ትግል እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ይሄ ከንቱ ድካሙ መቼም ቢሆን እንደማይሳካለት ተናግረዋል።

አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ያቆዩንን ሀገር እኛም አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያ ስጋት ወደማይሆን ደረጃ በማድረስ እንደግመዋለን ብለዋል።

ወይዘሮ ድግሴ መንግስቴ በበኩላቸውዳግም ወረራ የፈጸመብንን አሸባሪው ህወሓት ለመፋለም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድነት መነሳት ይኖርብናል ብለዋል።

ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች የጸጥታ አካላት ስንቅ ማዘጋጀትን ጨምሮ  አስፈላጊውን ሁሉ የደጀንነት ተግባር ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ህዝብ የሽምግልና ስርዓት ማህበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን በበኩላቸው ''የተጋረጠብንን ፈተና ለማለፍ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን በአንድነት መቆም አለብን'' ብለዋል።

ወኔን በመሰነቅና አንድ በመሆን በጥበብና በብስለት የጠላትን ወረራ መቀልበስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በተካሄደው የውይይት መድረክም ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም