የኦሮሞ ጀግኖች ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ያበረከቱትን አኩሪ ታሪክ የሚያትት "ደንበሊ" የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

ነሃሴ 29/2014/ኢዜአ/ የኦሮሞ ጀግኖች ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ያበረከቱትን አኩሪ ተጋድሎና ጀብዱ የሚያትት "ደንበሊ" የተሰኘ የታሪክ መጽሐፍ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።

በመጽሐፉ ምርቃት ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ብርቱካን አያኖ፣ የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ የተደረሰው ይህ መጽሐፍ የቀኝ አዝማች ተሰማ ገላን እና የሜታ አርበኞችን ታሪክ የሚያትት ሲሆን በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ተሰናድቷል።

"ደንበሊ"  ወይም በአማርኛ ማዕበል የሚል አቻ ትርጉም አለው፤  መጽሐፉ የኦሮሞ ጀግኖች ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ያበረከቱትን አኩሪ ተጋድሎና ጀብዱ በማሰባሰብ በታሪክ ይዘት ተከትቦ ለተደራሲያን ገበያ ላይ ቀርቧል።

በ404 ገፆች የተቀነበበው ይህ የታሪክ መፅሐፍ ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ ቋንቋም እንደተዘጋጀ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም