አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተብንን ጦርነት በጋራ ለመመከት ዝግጁ ነን- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተብንን ጦርነት በጋራ ለመመከት ዝግጁ ነን- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
ነሐሴ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከመከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ቁርጠኛ መሆናቸውን የደሴ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይቷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አማረ እሸቱ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን ጠቁመው፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመሆን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ለመጠበቅና የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ዋጋ እየከፈሉ ከሚገኙት የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ጠላትን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
''የሽብር ቡድኑበሚነዛው የሀሰት ወሬ ሳንደናገጥ ስንቅና ትጥቅም እናቀብላለን፣አካባቢያችንንም ከሰርጎ ገቦች በመጠበቅ ነፃነታችንን በደምና አጥንታችን ጭምር እናረጋግጣለን'' ብለዋል።
ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሞሚና አደም አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የሠላም አማራጭ ወደ ጎን በመግፋት ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት በጋራ እንደሚመክቱ ተናግረዋል።
የስንቅ ዝግጅት በማድረግ ደጀንነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከሽብር ቡድኑ ጋር የጥቅም ትስስር ፈጥረው በፈጠራ ወሬ ህዝብ የሚያወናብዱና የጀግናውን መከላከያ ሠራዊትን ስም የሚያጠልሹ ሴረኞች መኖራቸውን አመልክተው፤መንግሥት አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
''ለመስራትም፣ለማምለክም፣ለመኖርም ቅድሚያ ሰላማችን መረጋገጥ አለበት'' ያሉት ወይዘሮዋ፤ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን የኢትዮጵያን ሰላም እናረጋግጣለን ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው የአሸባሪውን ህወሓት ወረራ በጋራ በመመከት የኢትዮጵያን ህልውና ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ጦርነቱን ለመመከት በእልህና በቁጭት መነሳቱን ጠቁመው፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ስም በሚያጠልሹና የሐሰት ወሬ በሚነዙት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
በጥቅም ትስስር የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ለማስፈፀም የሚሯሯጡ አካላት መኖራቸውን ያስረዱት አቶ ሳሙኤል፤ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን የማጋለጥና ሰርጎ ገቦችን የመከላከል ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላትን በመደገፍ ደጀንነታችንን በተግባር እናረጋግጣለን ብለዋል።
የአማራ ክልል የበይነ መንግስታት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደስታ ተስፋው በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት የሰላም በሮችን ዘግቶ ዳግም ወረራና ጦርነት በመጀመሩ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እየመከተው መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ አሸባሪውን ህወሓት የመመከቱን ተግባርማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል።