ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አሳሰበ
ሐዋሳ፤ ነሐሴ 29/2014 (ኢዜአ)፡ ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ሀጂ ኢብራሀም ቱፋ አሳሰቡ።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና የምክር ቤቱ አባላት ከሲዳማ ክልል የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር ዛሬ በሐዋሳ አካሂደዋል።
ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ሀገር ካለባት የሰላም እጦት እንድትላቀቅ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመተባበር መስራት አለበት።
''እምነት የሚኖረው ሀገር ስትኖር ነው'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ "በአሁኑ ሰዓት ከምንም በላይ የሚያስፈልገን እርስ በእርስ መረዳዳት፣ ፍቅርና አንድነት በመሆኑ የእስልምና እምነት በሚያዘው መሰረት ህዝበ ሙስሊሙ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መስራት ይጠበቅበታል" ብለዋል።
የሲዳማ ህዝብ በህብረት አንድ ሆኖ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በፍቅር መኖሩ ክልሉን ትንሿ ኢትዮጵያ አሰኝቶታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን ከአንድነት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ያሉት ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ''የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድምና እህቶቻችሁ ጋር በፍቅርና በአንድነት መኖር አለባችሁ" ሲሉ አሳስበዋል።
የእስልምና እምነት ተከታዮች በቅርቡ ባደረጉት ሰላማዊ ምርጫ የተመረጡት አዲስ የምክር ቤት አመራሮች ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አንድነት የክልሉ እስልምና እምነት ተከታይ አንድ ሆኖ የሚጠበቅበትን እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው" ያሉት ሀጂ ናስር፤ ከእስልምና አስተምህሮት ጎን ለጎን የእምነቱን ተከታዮች ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ህዝቦች አንድነትና ፍቅር የማስተማር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በትውውቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች፣ የምዕራብ አርሲ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሲዳማ ክልል እስልምና እምነት ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች መሳተፋቸው ተመላክቷል።