ሀገር በማፅናትና በማስቀጠል ሂደት ዳያስፖራው ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በመረዳት ለሀገራዊ ጥሪው ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በማፅናትና በማስቀጠል ሂደት ዳያስፖራው ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በመረዳት ለሀገራዊ ጥሪው ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል
ነሐሴ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ)ሀገር በማፅናትና በማስቀጠል ሂደት ዳያስፖራው ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በመረዳት ለሀገራዊ ጥሪው ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገልጿል፡፡
“የጸና ሀገረ መንግስት ዜጎች በየወቅቱና በየዘርፋቸው በሚከፍሉት መስዋዕትነት እንደሚፈጠር ታሪክ ያስተምረናል “ብሏል አገልግሎቱ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት፣ “ኢትዮጵያውያንም ሀገረ መንግስታቸውን ለማጽናትና ለማስቀጠል በዘመናት መካከል አያሌ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ዛሬም በመክፈልም ላይ ይገኛሉ።
ለዚህም ነው ሀገር ማፅናትና ማስቀጠል የሁሉም ዜጎች የሁል ግዜ ተልዕኮ ነው የሚባለው” ብሏል፡፡
ዜጎች ሀገር በማፅናት ሂደት በሚና አይነት የሚለያዩ ነገር ግን አንዱ በአንዱ የማይተካኩ ድርሻዎች አሏቸው ያለው አገልግሎቱ፣ ወታደር በላብ፣በደም እና በአጥንት ሀገር የማስቀጠል ተልእኮውን ሲወጣ የተቀሩ ዜጎች በሌላኛው ግንባር የሀገርን ሰላም፣ ክብርና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ ለተመሳሳይ ሀገር የማፅናት ተልእኮ ሊሰለፉ ግድ እንደሚል ገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የወታደሮቿ ላብ፣ ደምና አጥንት ያጸናት ሀገር መሆኗን አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ በተሰማሩና በሚከፍሉት መስዋዕትነት ለሀገራቸው ወታደርነታቸውን ባረጋገጡ ልጆቿ ጸንታ የኖረች ሀገር እንደሆነች ገልጿል።
መግለጫው ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ያልተገቡ ጫናዎችንና ጥቃቶችን ለመመከት ያደረጋቸውን ልዩ ልዩ ተጋድሎዎች ዘርዝሮ፣ ክስተቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደማቁ መጻፉን አውስቷል።
ዛሬም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለማዋረድ የሚፈልጉ ጠላቶቿ የከፈቱትን አዲስ ጥቃት ለመመከት ሰራዊቱና ህዝቡ በመዋደቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በዚህ የፈተና እና የድል ጉዞ ወቅት ዳያስፖራው ዘርፈ ብዙ ተሳትፎውን ዳግም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።
“ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ለኢትዮጵያ የሚቆምበት ጊዜም አሁን ነው፡፡ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበርና የውስጥ ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዳያስፖራው ትልቅ ኃላፊነት አለበት” ብሏል አገልግሎቱ፡፡
የልማት ሥራዎቻችንና ፕሮጀክቶቻችን እንዳይቆሙ፣ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎቻችን እንዲቀላጠፉና ሰብአዊ ድጋፎች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን እንዲደርሱ ዳያስፖራው የማይተካ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ተብሏል፡፡
በተለይም የውጭ ምንዛሪ አቅምን ለማሳደግና ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀገር የማስቀጠል አንዱን ዘርፍ ለማገዝ ዳያስፖራው ሰፋፊ የሀብት ማሰባሰቢያ ንቅናቄዎችን በማካሄድ ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ እንዲልክና ለሀገራዊ ጥሪው ምላሽ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል፡፡
አገልግሎቱ ዳያስፖራው ከዚህ በፊት ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲውሉ መንግስት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የከፈታቸውና ዳያስፖራው ሲጠቀምባቸው የነበሩ አካውንቶችን ማለትም ለዩሮ (1000439142832)፣ ለዶላር (1000439142786) እንዲሁም ለፓውንድ (1000443606304) በመጠቀም የተለመደ አለኝታነቱን ዳግም በማረጋገጥ ለሀገሩ ዘብ እንዲቆም ይጠይቃል።