ኢዜአ የሀገር ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የሀገር ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገለፀ
ነሀሴ 28/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሀገር ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የተቋሙ አመራሮች ገልፀዋል።
ተቋሙ በህግ ማስከበር ዘመቻው የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ጋዜጠኞችን ለቀጣይ ተልእኮ ዝግጁ ማድረግን ያለመ የእውቅና መርሃ-ግብር አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች በተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተቋማዊ ግንባታ እና በይዘት ስራዎች እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ማሻሻያ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸው ተነስቷል።
ተቋሙ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን የአገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይ አድማሱን በማስፋት በውጭ ሀገራት ወኪሎች እንዲኖሩት መታቀዱ ገልጿል።
በመድረኩ ተቋሙ በህግ ማስከበር ዘመቻው የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ጋዜጠኞችን ለቀጣይ ተልእኮ ዝግጁ ማድረግን ያለመ የእውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብር አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እንደተናገሩት፤ተቋሙ በግንባር በሙያቸው አስተዋፆ ያደረጉ ጋዜጠኞቹን እውቅና ሲሰጥ ቀጣዩን ተልዕኮ ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ኢዜአ እንዲሰራ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲወጣ ውጤታማ ባለሙያዎችን እውቅና መስጠትና ማበረታታት ይገባል ነው ያሉት።
የእውቅናው ዓላማ ያለፈውን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን ቀጣዩን ተልዕኮ ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረው፤ ኢዜአ የሀገር ሉዓላዊነት የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ አመራር ቦርድ አባል ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው ኢዜአ ተልዕኮውን እና የይዘት ስራዎቹን አመጣጥኖ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ኢዜአ አሁን ላይ ያገኘውን ስም እና ተዓማኒነት በዘላቂነት አስጠብቆ ለመሄድ ጥራት ያላቸው ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተቋሙ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካ በአግባቡ በማጥናትና በመተንተን የራሱን ልዩ ሚና የሚወጣ ጠንካራ ተቋም መሆን አለበት ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሀገር መከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ ኢዜአ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሙያው ላደረገው ሚና አመስግነው ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አንድነት በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው የገለፁት ኮሎኔል ጌትነት፤ ኢዜአ በዚሁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ነው የጠቆሙት።
አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ ኢዜአ የሀገሪቱ ብቸኛ የመረጃ ምንጭና ቋት ሊሆን እንደሚገባው ገጿል።
ተቋሙ አሁን የጀመረውን ስኬታማ ጉዞ አጠናክሮ ከቀጠለ ዓአለም አፍቀ የሚዲያ ተቋማት ጋር ብቁ ተወዳዳሪ የመሆን ሰፊ እድል እንዳለው ጠቁሟል።