ቀጥታ፡

ለኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል የ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሶች ድጋፍ ተደረገ

ደሴ ፤ ነሐሴ 28/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን ያስረከቡት በማህበሩ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ግርማይ እንደገለጹት፤  ማህበሩ ድጋፉን ያደረገው ሆስፒታሉ ያሉበትን የህክምና ቁሳቁስ ግብዓት እጥረት ችግር ለማቃለል ነው።

የህሙማን ተኝቶ   መታከሚያ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ ብርድ ልብስ፣ የተለያዩ መድሃኒቶችና ሌሎችም የህክምና ቁሶች ከተደረጉት ድጋፎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

ማህበሩ ዛሬ ያደረገውን 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሶች ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጠል  አስታውቀዋል፡፡

የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ይመር በበኩላቸው፤  ሆስፒታሉ ባለፈው ዓመት በአሸባሪው ህወሓት ውድመት ቢደርስበትም በቅንጅት በተደረገው መልሶ መቋቋም ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ የነበረበትን ችግር እንደሚያቃልል ጠቅሰው ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሆኖም  በግብዓት እጥረት በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ ባለመሆኑ ሁሉም በሚችለው ልክ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሆስፒታሉ በተሻለ ደረጃ መልሶ ተቋቁሞ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ውብሸት  ብርሃኑ  ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያደረገው ድጋፍ ለሆስፒታሉ ስራ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሌሎችም   እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ለደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችና አፋር ክልል በከፊል ጨምሮ ከ1 ነጥብ  5 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ተደራሽ እንደሆነ የኢዜአ ሪፖርተር የሆስፒታሉን አስተዳደር በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ ከደሴ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም