የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን የእግር ኳስ ውድድር አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን የእግር ኳስ ውድድር አለፈ
ነሐሴ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በአልጄሪያ አስተናጅነት ለሚካሄደው ሰባተኛው የአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ ለሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ማለፉን አረጋገጠ።
ብሔራዊ ቡድኑ 10 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሁዬ ስታዲየም ዛሬ ከርዋንዳ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዳዋ ሁቴሳ በ22ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ውጤቱን ተከትሎ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋልያዎቹ በድምር ውጤት 1 ለ 0 በማሸነፍ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በጥር ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው ሰባተኛው የቻን የእግር ኳስ ውድድር ትኬታቸውን ቆርጠዋል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በታንዛንያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ዋልያዎቹ በቻን የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 5 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተሳታፊዎች ቁጥር በመጨመር ከዚህ ቀደም በሻምፒዮናው የሚሳተፉ 16 አገራትን በአልጄሪያው ውድድር ወደ 18 ከፍ አድርጓል።