ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያዊያን እውነተኛ ኩራት ሆኖ ይቀጥላል! - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያዊያን እውነተኛ ኩራት ሆኖ ይቀጥላል!

ነሀሴ 28/2014 /ኢዜአ/ ተግዳሮቶቹን በድል ተሻግሮ ለኢትዮጵያ የብርሃን ተስፋ የፈነጠቀው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያዊያን እውነተኛ ኩራት ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን የተባባረ ክንድ ተገንብቶ ብርሃን ሊሰጥ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋዩ ተቀመጠ፡፡
አባይ ለዘመናት ለኢትዮጵያ የረባ ጥቅም ሳይሰጥ ወደ ጎሮቤት አገራት የሚሰደድ፣ የሚታይ እንጂ የማይበላ እንጀራ ሆኖ መቆየቱም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
አባይ ወደ ብርሃንነት እንዲቀየር ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍላጎት የመሰረተ ድንጋዩ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ በመደገፍ አሳይተዋል፡፡
ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከደሃ እስከ ሃብታም፣ ከህጻን እስከ ሽማግሌ፣ ከምሁሩ እስከ አልተማረው እንዲሁም በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው በመዋጣት እንደ ዓይን ብሌናቸውም ሲጠባበቁት ነበር፡፡
ህዝቡ በእልህና ቁጭት ያዋጣውን በርካታ ገንዘብ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት ሲበሉና ሲበዘብዙ መቆየታቸውም ይታወቃል፡፡
ለህዳሴ ግድቡ ተብሎ ህዝብ የሚያወጣው ገንዘብም የግለሰቦችን ኪስ ከማደለብ ባለፈ እንደተፈለገው ግድቡን በፍጥነት ማጠናቀቅ ሳይችል ቀረ፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ቀዳሚ ትኩረቱ ከሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኛው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡
በዚህም በቀደመው የይስሙላ የግንባታ ዓመታት በግድቡ ላይ የነበሩ በርካታ ችግሮች ላይ የማሻሻያ ሥራዎች በመስራት እነሆ ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር ማድረግ ተችሏል፡፡
የለውጥ መንግስቱ የህዳሴ ግድቡን እውን ማድረግ በጀመረበት ወቅትም መቀሌ የመሸገው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የተለያዩ አሉባልታዎችንና የሃሰት መረጃዎችን ማሰራጨት የግድቡ ግንባታን ጥላሸት ለመቀባት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ወትሮውንም የኢትዮጵያን ህዝብ በመዝረፍ የሚታወቁት የቡድኑ ቁንጮ አመራሮች "ግድቡ ተሽጧል" በሚል የሃሰት ትርክት በማሰራጨት ህዝቡን ማወናበድ ጀምሩ፡፡
ነገር ግን የለውጡ መንግስት የአባይ ወንዝ ከጉባ ተራሮች ግርጌ ኃይል እንዲያመነጭ በማድረግ የሽብር ቡድኑ የሃሰት ዘመቻ ከንቱ መሆኑን በተግባር ማሳየት ችሏል፡፡
በዚህም "ግድቡ ተሽጧል" በሚል በአሸባሪው የህወሃት አፈቀላጤዎች ሲነዛ የነበረውን ዘመቻ በማክሸፍ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስራን በድል ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ጫና ቢኖርባትም በህዳሴ ግድብ ላይ የምታከናውነው ስራ ለሰከንድ ሳታቋርጥ ዛሬ ላይ ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር " የህዳሴ ግድቡ ብዙ እየተፈተንበት ያሉ ነገሮች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባነው መሰረት እናሳካዋለን " ብለው በተናገሩት መሰረትም ቃላቸውን በተግባር መፈጸም ችለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንጨርሰዋለን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የምንጨርሰው ልጆቻችንን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስም እንደምንችል እንዲያውቁት ስለምንፈልግም ጭምር ነው" በማለት መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የአባይ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን በከፍተኛ ወኔ ሲደግፈው እንደነበር ሁሉ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ በመድረሱም ደስ መሰኘቱን ተናግረዋል፡፡
"ህዝቡ ከፍተኛ ተስፋ የጣለበት ግድብ ነው" የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ፤ አሁን የደረሰበት ደረጃ ለህዝቡ ልፋት ውጤት ያጎናጸፈ ነው ይላሉ፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገራችን በርካታ ፈተናዎች የገጠሟት ቢሆንም ፕሮጀክቱ ግን ለአፍታም ሳይቆም አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ የሚገጥሟቸውን ችግሮች እየተሻገርን እዚህ ደርሰናል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ለግድቡ እዚህ ደረጃ መድረስ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብና በተባባረ ክንድ ሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
የሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ከጉባ ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አባይ የኢትዮጵያ ኩራት፣ የብልጽግና ጅማሮ መነሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አባይ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ከፍታ የሚለመልምበት ቦታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም እንደቀደመው ሁሉ በጋራ ለሌላ ድል መስራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"የተጀመረው ድል ይቅጥላል፣ የሚገጥሙን ፈተናወችም የሚያሸንፉን ሳይሆን ይበልጥ የሚያጠነክሩን ይሆናሉ" ሲሉም ነው የጠቆሙት፡፡
ተግዳሮቶቹን በድል ተሻግሮ ለኢትዮጵያ የብርሃን ተስፋ የፈነጠቀው ህዳሴ ግድብ በአዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያዊያ እውነተኛ ኩራት ሆኖ እንደሚቀጥል በለውጥ ዓመታቱ የተሰሩት ስራዎች ማሳያ ናቸው፡፡
የህዳሴ ግድቡ በአዲሱ ዓመትም የኢትዮጵያዊያን ብሩህ ተስፋ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ካሉት 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል የመጀመሪያው ተርባይን የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።