ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንሳዊ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት በመሆን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንሳዊ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት በመሆን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል
ጎንደር (ኢዜአ) ነሐሴ 28/2014 ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንሳዊ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት በመሆን ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ተናገሩ፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 5ሺህ 527 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሮፌሰር ተከተል እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎትን በማሟላትና የትምህርትና የምርምር ጥራትን በማሳዳግ ለሀገሪቱ እድገት መፋጠን ድርሻቸው የላቀ ነው።
በኢትዮጵያ ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ተከተል፣ ተቋሙ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርምር ቤተ-ሙከራዎችን እና ሰርቶማሳያዎችን በማደራጀቱ በምርምር ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"የሳይንስና ቴክኖሎጂ አሁን ባለንበት ዘመን አስፈላጊነት እየጎላ መጥቷል" ያሉት ፕሮፌሰር ተከተል፣ በትምህርት፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለምአቀፍ ውድድሩን ለመቀላቀል ዩኒቨርሲቲዎች ሚናቸው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ተከትል እንዳሉት የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎችን በሀገር ውስጥ ማሳደግ፣ ማዘመንና ማሻሻል ያስፈልጋል።
ሀገር በቀል እውቀቶችን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር በመጠቀም በኩል ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዛሬ ምሩቃንም በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ታግዘው ለአዳዲስ ፈጠራዎች ትኩረት በመስጠት በቴክኖሎጂ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
"የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራሱን በየጊዜው እያሳደገ በሀገራችን ብሎም በአፍሪካ ተመራጭ የምርምር ተቋም እየሆነ መጥቷል" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በጤና፣ በግብርናና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አተኩረው የሚሰሩ 19 የምርምር ማዕከላት እንዳሉትም ጠቁመዋል።
ተቋሙ በህግ ትምህርት ቤቱ አማካኝነት ነጻ የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ተጋላጭ ለሆኑ ከ1ሺህ 100 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል።
በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግና በጦርነቱ የተጎዱ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣቱንም ገልጸዋል።
ከእለቱ ተመራቂዎች መካከል 3 ነጥብ 99 በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ ሰውአረግ አረጋ፣ "ከተማሪ ስኬት ጀርባ ያሉትን ወላጅና ሀገር ውለታቸው ሳይረሳ ኢትዮጵያንና ወገንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እንስራ" ብላለች።
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ሁለት ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።